Thursday, June 26, 2008

"የቅራኔ መፍቻ ዘይቤያችን ችግር አለው ወዳጄ!"

ጥንታዊነት ህዝቦችን የሚያስተሳስር ድርና ማግ የመፍተል ችሎታ ያለውን ያህል በአንጻሩ ደግሞ በጎሪጥ የሚያስተያይና ውስብስብ ቁርሾ ጥሎ የማለፍ መዘዝም አለው።

ቅራኔዎቻችንን ፈትተን ወደተረጋጋ የልማት እንቅስቃሴ መጣደፍ አለብን የምንል ሁሉ በሚያስትሳስሩን ድሮች ላይ መደስኮሩን ቀነስ አድርገን ለስጋቶቻችንንና ለቁርሾዎቻችን መነሻ የሆኑትን የታሪክ ጭብጦች አፍጠርጥረን በማውጣት ለጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት መዘጋጀት አለብን። እስካሁን እንዳየሁት የቅራኔ ፍች ጥረቶቻችን ወይንም ሃቀኝነት የጎደላቸው፤ ወይንም ብልሀቱ የጠፋቸው ነበሩ።

የጁዲዮ-ክርስቲያኑም የእስልምናውም የሀይማኖት መሠረታችን ነገርን ጠበቅ አርጎ የማየት በህርይ አለውና ብዙዎቻችን ዓለምን የምናያት በጽድቅና በኩነኔ፤ በብርሀንና በጨለማ፤ በበጎና በክፉ፤ በበዳይና በተበዳይ እየፈረጅን ነው። መሃል ላይ ሌላ ውብ ዓለም እንዳለ መቀበል ያዳግተናል። በማህበረሰብም በግለሰብም ደረጃ ይህ አመለካከት ከተንጸባረቀ የሚገልጸው ኋላቀርነታችንን ነው።

ስለ ዘመናዊ ቅራኔ መፍቻ (ኮንፍሊክት ሬዞሉሽን) ዘዴዎች አንዳንድ ነገር ከማለቴ በፊት ከወዲሁ ግልጽ የማደርገው ነገር የ “አንተም ተው አንተም ተው” ባህላዊ ሺምግልና ጊዜው ያለፈበትና ጊዜን አባካኝ መሆኑን ነው። ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሀቅ የባህላዊው ሽምግልና ደቀ-መዝሙር መሆናቸውን ስለማውቅ ከኔ ጋር ባይስማሙ አልደነቅም። የሀያ አንደኛው ክፍለዘመን ችግር ሊፈታ የሚችለው በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ዘዴዎች መሆን አለበት ለማለት እንጅ ለባህላችንም ለፕሮፌሰር ኤፍሬምም ከበሬታ አለኝ።

የቅራኔ መነሻዎች
-ሳይፈቱ የቆዩ ቅራኔዎች ወይንም ቁርሾዎች
-ለክብር፤ ለሥልጣንና ለዕውቅና ያለ ፍላጎት ሳይሟላ ሲቀር። (እነዚህን ፍላጎቶች በሠላማዊና -ገንቢ በሆነ መንገድ ለማሟላት ሳይቻል ሲቀር)
-የህልውና፤ የሥልጣን፤ የንብረት፤ የግንኙነትና የመሳሰሉት ገደቦች በግልጽ ሳይቀረጹ ሲቀር ወይንም በቂ መስለው ሳይታዩ
የቅራኔ መፍቻ ዘዴዎች
-የግንኙነቶችን ዳር ድንበር በግልጽ መከለል ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ወግ እንዲኖረው ያደርጋል።
-የራስንም ሆነ የባላንጣን ፍላጎት በቅድሚያ አንጥሮ ማወቅ ወደድልና ወደስምምነት ያመራል። የራስን ጥቅምና ምኞት ሳይጎዱ የባላንጣን ፍላጎት ለማቻቻል በአርምሞ ማሰብ ተገቢ ነው።
-ግልጽ ጠቀሜታ ከማይታይበት የስምምነት ሀሳብ ውጤት መጠበቅ አይቻልም። ሌላውን ወገን ምን እንደሚያጓጓው ማወቅና ትብብሩን የሚመጥን ማካካሻ ማውጠንጠን ብልህነት ነው።
-የሌሎችን ስጋት ሲቻል የሚያጠፋ አለያ ደግሞ የሚቀንስ አስታራቂ መንገድ ማሰላሰል ትልቅነት ነው።
-በድርድር ጠረጴዛ ላይ የዕብሪት፤ የስጋት፤ የሺንፈትና የብልጣ-ብልጥነት መንፈስ ከተንጸባረቀ ጥረቱ ውጤት አልባ ይሆናል። የትብብርና የመከባበር ዓየር ሊፈጠር ይገባል።
-ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት የኃይል ሚዛን መቀየስ አስተውይነት ነው።
-አሉታዊና አወንታዊ ውጤቶችን ከበቀል ነፃ በሆነ መንገድ የሚቀበል ባህል መዘርጋት
አቋምን ለመቀየርም ሆነ ለማስተካከል የሚያበረታታ የ “ክፍት በር” ፖሊሲ ማዳበር

ስለ ዘመናዊ የቅራኔ አፈታት ዘዴዎች ለማወቅ በየቦታው የቃረምኩት እውቀት በርካታ ነው። ያነበብኳቸው ታሪኮችም ጉደኛ ናቸው። ታዲያ በሁለት ገጽ መጣጥፍ ማጠቃለል አይቻልምና እንዲች ብየ አልሞክረውም። ትንሽ ዕውቀት አደገኛ ናት እንዲሉ የለቃቀምኳትን ዕውቀት አንግቤ ነገር ማውጠንጠን ጀመርኩ። ከቶ የኢሕአዴግ ችግር ምንድነው አልሁ። ምን ቢሆን ነው እንዲህ በርጋጊ፤ እንዲህ ቁጡ፤ እንዲህ ተጠራጣሪ፤ እንዲህ እብሪተኛ የሆነው? የሚለውን። አቶ አዕምሮ እንዲህ ሲል መለሰልኝ ስለ ኢሕአዴግ ስጋቶችና ፍላጎቶች….

የኢሕአዴግና የመለስ ዜናዊ ስጋቶች
-የአነስተኛ ብሔረሰቦች መብትና ጥቅም በታላላቅ ብሔረሰቦች ይዋጣል
-ዴሞክራሲ የቁጥር ድምር ውጤት ስለሆነ አነስተኛ ብሔረሰቦች የስልጣን እርካብን መርገጥ ይሳናቸዋል
-የአነስተኛ ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል በታላላቅ ብሔረሰቦች ቋንቋና ባህል ይዋጣል
-የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረው ቦታ ይኮስሳል
-የትግራይ ሕዝብ ባለፉት 40—50 ዓመታት የደረሰበት ጉስቁልና (ግስቁልናን ለትግራይ ብቻ ማን እንደሰጠው ባላውቅም) እንዳይደገም ማረጋገጫ ይፈልጋል
-በኤርትራ መገንጠል፤ አሁን ደግሞ ለሱዳን በተሰጠው መሬት ላይ ተጠያቂነትን ይፈራል
-በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በከንቱ ለጠፋው ሕይወት ተጠያቂነትን ይፈራል
-የትግራይ የልማት፤ የንግድና የኢንዱስትሪ ድርጅቶች በመንግሥት አድሎዋዊነት ያጋበሱት ሀብት ይወሰዳል ብሎ የሰጋል
-ለመንበሩ ቀረብ ያሉ የትግራይ ተወላጆችና ሌሎች ዳረጎተኝች በአጭር ጊዜ ውስጥ ያጋበሱት ሀብት አደጋ ላይ ይወድቃል ብሎ ይሰጋል
-ቅንጅት/አንድነት ፓርቲ በመላ አገሪቱ ውስጥ ተቀባይነት ማግኘቱ የኢሕአዴግን የፖለቲካ ጭብት ያመነምነዋል ብሎ ይፈራል
-ካላቸው የሕዝብ ብዛት አንጻር የአማራና የኦሮሞ ፓርቲዎች ትብብር ለሕውሀት/ኢሕአዴግ አስቸጋሪ የፖለቲካ ዘመን ያመጣል ብሎ ይሰጋል

የኢሕአዴግና የመለስ ዜናዊ ፍላጎቶች
-አነስተኛ ብሔረሰቦች (ስጋቶች እስኪጠፉ ድረስ) እኩል ሚና እንዲኖራቸው የሚያደርግ የፖለቲካ ድርድር
-ወያኔ አርነት ትግራይና የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ዓቢይ ቦታ ይዘው እንዲቆዩ ማድረግ። የይገባኛል አበሳ
-በአንጻራዊ ደረጃ ያልዳበረ የልማት መሠረት ያላቸው አካባቢዎች ፕሪፈረንሻል ትሪትመንት እንዲኖራቸው ማድረግ
-በወያኔ አገዛዝ ዘመን ለተካበተ ድርጅታዊና ግለሰባዊ ሃብት ማረጋገጫ ማግኘት
-በወያኔ ዘመን ለተወሰዱ ውሳኔዎች ከተጠያቂነት የሚያድን ማረጋገጫ
-መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት አባት የመባል ምኞት
-መለስ ዜናዊ የአዲሲቱ አፍሪካ ባለራዕይ ተብሎ የመሰየም ጉጉት
-መለስ ዜናዊ ከ 2005 ምርጫ በኋላ ያጣውን የታላላቅ መንግሥታት እቅፍ ማግኘት

ካለው መንግሥት ጋርም ሆነ በተቀናቃኝ ፓርቲዎች መሀከል ያሚታየውን አለመግባባት ለመፍታት የፖለቲካ ድርድር አያልፉት ዓይነት አባዜ ነው። ጽሁፌን ከሁለት ገጽ ላለማስበለጥ ለራሴ የገባሁትን ቃል ማክበር አለብኝና በዚህ ጎዳና እንጓዝ ካልን መጠየቅ ካለባቸው ጉዳይች አንዳንዶቹን በግርድፉም ቢሆን አቅርቤያለሁ። ውይይት ከፈለጋችሁ በሩ ክፍት ነው።

kuchiye@gmail.com

No comments: