Friday, July 31, 2009

"መድረክ እንዲህ ሊያናቁር ይገባል?"
በአንድነት ፓርቲ ዙሪያ የሚናፈሰው ውዝግብ ወርደ-ሰፊ ትምህርት ያዘለ ነው።

ትምህርቱ ለፓርቲው ሀላፊዎችና ደጋፊዎች ብቻ ባድራሻ የተላከ ሳይሆን ባገራቸው ፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ሁነኛ ለውጥ እናመጣለን ብለው ለሚባዝኑ ሌሎች ፓርቲዎች ጭምር የሚተርፍ ይመስለኛል። ከዲስኩር ላድናችሁ ብዬ ነው እንጅ በዚህ ዙሪያ ብዙ የምለው ነበረኝ።

አንድነት ውስጥ አሁን ለተፈጠረው ውዝግብ መነሻ የሆነው “መድረክ ውስጥ እንግባ አንግባ? የምንገባስ ቢሆን ምን ዳር-ድንበር አስቀምጠን ቢሆን ይሻላል?” የሚለው ነው። ሌሎች በበራሪ ወረቀት የሚበተኑ ክሶችና ሀሜቶች በተረፈ-ፖለቲካና በማድቤት ወሬነት የሚመደቡ ናቸው።

መድረክ በመሠረቱ፤
ማንም ይጀምረው ማን መድረክ ያለፈው 18 ዓመት የተዛባ የፖለቲካ ጉዞ የፈጠረው ህዋስ ነው። ዘረ-መል (ጄኔቲክ) ምንጩ የተለዬ ነውና ቀደም ባለው ዘመን ከተፈጠሩ ስብስቦች ጋር በመሳ ሊታይ የሚገባው አይደለም።

መድረክ ከሚነቀፍባቸው ምክንያቶች፤
መድረክ ላይ ከሚሰነዘሩት ነቀፋዎች መሀከል ሁለቱንና ዋናዎቹን ላንሳ። (ሀ) መድረክን የመሠረቱት የብሔር ድርጅቶች ናቸው፤ (ለ) መድረክ ውስጥ ሕዝባዊና ድርጅታዊ መሠረት የሌላቸው ግለሰቦች ተሰንገዋልና እነሱን ከድርጅት ጋር መሳ ማዬትና መወጣጫ እርካብ ማቀበል ጅልነት ነው የሚሉት ናቸው።

የብሔር ድርጅቶች የሆኑ እንደሆንስ?
ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ድርጅቶችና የብሔር ስሜት የለም ብሎ ራሱን የሚያታልል ካለ በዚህኛው ክፍለዘመን የሚኖር አይደለም። የቱን ያህል ዘግናኝ ቢሆንም ያገራችን የፖለቲካ እውነታ የብሔር ቅኝት አለው። የቅኝቱ ቁስል መንግሥት ባለፉት አሥራ ስምንት ዓመታት ባካሄደው የተሳሳተ ዘመቻ ይበልጥ እንደሰፋ መዘንጋትም ስህተት ላይ ይጥላል። አንድ የዩኒቨርሲቲ መምህር በቅርቡ የገጠመውን ግራ መጋባት ላጫውታችሁ። መምህሩ በንግሊዝኛ አነበነበና ተማሪዎቹ ገብቷቸውና አልገባቸው እንደሆነ ጠየቀ። ጭንቅላቶች ግራና ቀኝ ተወዛወዙ። ችግሩ የንግሊዘኛ ቋንቋ ችሎታ መሆን አለበት አለና ትምሕርቱን በብሔራዊ ቋንቋው ባማርኛ ደገመውና ተከትለውት እንደሁ ጠየቀ። ጥቂት የማይባለው ክፍል አሁንም እንዳልተከተለው ተረዳ።

የመምህሩን ልምድ ከብዙ አኳያ ልንተነትነው የምንችል ቢሆንም ከጽሁፌ ዓላማ አንፃር ዓይኑን ያፈጠጠብኝ ነገር አለ። የብሄርን ጉዳይ የምንፈታው አግልለነው ሳይሆን ወደጉያችን ጠጋ አድርገን መሆኑን ነው። ባዲስ አመለካከትና በብልህ ስሌት መልክ ካልያሳዝነው አገራችን የምታመራበት አቅጣጫ እጅጉን አያምረም። ለዚህ ነው መድረክ ውስጥ ገብቶ መሥራትም ሆነ በተወሰነ ደርጃ ተሻርኮ መንቀሳቀስ ትክክለኛ የፖለቲካ አማራጭ መስሎ የሚታዬኝ።

ሌላም ልንስተው የማይገባን የፖለቲካ ቁምነገር አለ። መድረክ ውስጥ ያሉት ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ይህን ያህል በብሔርተኝነት ልክፍት የተጠመዱ አይመስሉኝም - ያለፈው አሥራ ስምንት ዓመት የፖለቲካ ተመክሯቸው ብሔርተኝነት ለነርሱም ለክልሎቻቸውም ለኢትዮጵያም ጠቀሜታ እንደሌለው አስገንዝቧቸዋል የሚል ታሳቢ ማድረግ ይቻላልና። ከዚህም በተጨማሪ የምንኖርበት ዓለም ወደ ግሎባላይዜሺን መጣደፉ ትምህርት ሳይሰጣቸው ያልፋል ማለት ብልህነታቸው ላይ መሳለቅ ይሆናል አልሞክረውም።

“ታዲያ ይህ ከሆነ ድርጅቶቻቸውን ለምን ሕብረብሔራዊ አያደርጉም?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ አግባብነት አለው። ወገኖቼ! ሁሉም ፖለቲካ መንደራዊ ነው የሚለውን ብሂል መዘንጋት የለብንም። ፌደራላዊው የፖለቲካ አወቃቀርና የባጀቱ አፈሳስስ አጉራ-ተኮር እንደመሆኑ መጠን እነዚህ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን የሚደርሱት በዚሁ መሥመር በመጓዝ ይመስለኛል። በፈረንጁ አገር እንደምናየው “ፌደራል መንግሥቱ ጋር ተሟግቼ መንገድ አሠራሁልህ...ወዘተ” ማለት የማይችል ፓርቲና ፖለቲከኛ ዳግም ላይመረጥ ነውና አንዳንድ ፖለቲከኞች ይህን መንገድ ቢከተሉና መራጮቸውን ለመቅረብ መንገዳችን ይህ ነው ቢሉ ልንደነቅም ልንነቅፋቸውም አይገባም። ለነገሩ ብንደነቅና ብንነቅፍ ምን ለውጥ እናመጣለን?

ትንሺ ላክልበት። ፓርቲዎች የብሔር ቅኝት ስላላቸው ብቻ ሁሉም የአንቅጽ 39 አሺቃባጭ ናቸው ማለት አይደለም። ሁሉም ክልላዊ አወቃቀርን ይደግፋሉ ማለት አይደለም። እንዲህ ዓይነት ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መሥራት ብሔራዊ አንድነትን ሊያስገኝ የሚችል አጀንዳ በመቅረጽ ረገድ በር ይከፍታል። ካልተነጋገሩና አልፎ አልፎም “የቢራ ዲፕሎማሲ” ካላካሄዱ መተማመን አይገኝም፤ ስውር ጥላቻንና ጥርጣሬን ማስወገድ አይቻልም። ዴሞክራሲያዊ ባህልን ለማዳበርም ሆነ ከውዝግብ ነፃ የሆነች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አይቻልም። ያችን የምታውቋትን ጥቅስ አሁንም ልድገማትና “የፖለቲካ መነሻውም መድረሻውም ንግግር ነው” ።

የታዋቂ ግለሰቦች ጉዳይ!
በመድረኩ ውስጥ በግለሰብ ደረጃ ከተሰባሰቡት መሀከል የስዬ አብርሃና የነጋሶ ጊዳዳ ስም ጎልቶ ይነሳል። ገብሩ አሥራት በአረና ትግራይ ጃንጥላ ሥር ይሁን እንጅ ስሙ በጅጉ ሲነሳ እሰማለሁ። ቀልዱን እናቁምና ሁሉም ሰው እኩል አቅም፤ እኩል ተደማጭነት፤ እኩል ዕውቅት፤ እኩል ልምድ እኩል ዝናና ግርማ-ሞገሥ የለውም። ባንድ በኩል “ሴሌብሪቲ” የምንላቸው አሉ በሌላ በኩል ደግሞ “እኛ” አለን። ምን ማድረግ ይቻላል? ጨካኝ ዓለም ናት!

ሁሉም እኩል ቢሆንማ ኖሮ እኔና ኃይሌ ገብረሥላሴ እኩል ልንደመጥ ነው፤ አንኳኩተን እኩል በር ሊከፈትልን ነው፤ በምርጫ ተወዳድረን ኃይሌን የማሸንፍ ዕድል አለህ ልትሉኝ ነው። ህልም!

እነስዬ መድረክ ውስጥም ሆኑ ከመድረክ ውጭም ሆኑ የሴሌብሪቲ ደረጃቸው የሚያስገኝላቸው የፖለቲካ እሴት አለ። የሚያመጡት ዕውቀት ልምድና ተከታይ አለ። ያሳለፉት ሕይወትም ሆነ በቅርቡ ዘመን የደረሰባቸው ጉስቁልና ስለራሳቸውም ስላገራቸውም ብዙ ያስተማራቸው አለ። ስለሌሎቹ አላውቅም እንጅ ስዬ አብርሃ በቪ.ኦ.ኤ ደህና ነገር ሲናገር ትዝ ይለኛል። ሙሉ በሙሉ አንጀቴን ባያርሰውም ገብሩ አሥራት ዋሺንግተን መጥቶ በተናገረው ላይ ማለፊያ ጅምር አይቸበት ነበር። ሰዎችን የምናቀርበውና የምናርቀው ብትናንት ተግባራቸው ብቻ እየመዝንን ከሆነ በማናውቀው ንግድ ውስጥ ተሰማርተናል ማለት ነው። በጨዋ ቤት ፖለቲካ የወደፊት ጥቅም ማስከበሪያና የወዳጅ ክበብ ማስፊያ መሣሪያ ነው። ባለጌ ቤት ደግሞ የቂም በቀል መወጫና የዜሮ ድምር ሙግት መንኮራኩር ይሆናል። ምድባችን ከባለጌዎቹ ጎራ እንዳይሆን አምላክን መማለድ ተገቢ ነው።

ከመዝጋቴ በፊት የምመኛቸውን ጥቂት ነገሮች ላካፍላችሁ። በትናንቱ ላይ የማላዘንና የቁርሾ አባዜያችን እንዲለቀን እመኛለሁ። ከዴሞክራሲያዊ ውይይት በኋላ በተደረጉ ውሳኔዎች ተገዥ መሆንን እንድንማር ልቦናችንን ይከፍትልን ዘንድ እመኛለሁ። ግለሰቦችም፤ ድርጅቶችም፤ መንግሥታትም የሚያመሩት ወደ ዝቅተኛው የውጤታማነት ዕድሜያቸው መሆኑን ይቀበሉ ዘንድ እመኛለሁ።
kuchiye@gmail.com
ማሳሰቢያ። አስፈላጊ ባይሆንም ከመድረክም ከተጠቀሱት ግለሰቦችም ጋር እውቅና እንደሌለኝ እገልጻለሁ