Thursday, September 24, 2009

አውራ የሌለው ምንም የለው! (No Leader no Glory!)


ሶሻሊዝም ካወረሰን መዘዝ አንዱ በ “ጋራ አመራር” ላይ ያለን የተወላገደ አስተሳሰብ ይመስለኛል። እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረስሁት ጥቂት የማይባሉ ማሕበራዊና ፖለቲካ-ቀመስ ድርጅቶችን አሠራር ካገናዘብሁ በኋላ ነው።

ተደጋግፎ መኖር የግድ ከሆነበት ዘመን ጀምሮ በ “አውራ” መመራት አማራጭ አልተገኘለትም። ይህ ታዲያ በሰው ልጅ ዘር ብቻ የተገደበ እንዳይመስላችሁ። እንደ ንብ በደመ-ነፍስ የሚንቀሳቀሱት ሳይቀሩ አውራ ከሌላቸው ጣፋጭ ማር ቀርቶ ደረቅ ቂጣ መጋገር ይሳናቸዋል። ልብ ብላችሁ ከሆነ “አውራዎች” አላልኩም - ባንድ ቤት ውስጥና ባንድ ወቅት አንድ አውራ ብቻ ነው ሊኖር የሚችለውና ነው።

ጥሩ አውራ የጠለቀ ትምህርት፤ የተመሰከረ ልምድ፤ በሀቅ ለማገልገልና በውጤቱም ለመኩራት የጋለ ፍላጎት ያለው ነው። የሰውና የማቴሪያል ኃይሎችን አነቃቅቶና አስተባብሮ መሥራት ይችላል። በቅጣት ፋንታ ሽልማትን ማነቃቂያ መሣሪያው ያደርጋል። የሰዎችን አመኔታና ድጋፍ የሚያገኘው በተግባሩ ምሳሌ ሲሆንና ለሚያገለግለው ሕዝብ ፍቅርና ከበሬታ ሲያሳይ እንደሆነ ያውቃል።

ታዲያ እንዲህ ያለ ችሎታና ሥነ-ምግባር ያለውን ሰው የሚፈልገው ብዙ ነውና የኛ እናደርገው ካልን ከመንገዳችን ወጥተን ልናግባባውና ምቹ የሥራ አካባቢ ልንፈጥርለት ግዴታ ነው። በራዕይና በአጠቃላይ መርሆች ላይ ስምምነት እስካለን ድረስ ስልት የመቅረጹንና ውሳኔ የመስጠቱን ሥልጣን ለመሪውና እርሱ ላዋቀረው ቡድን መተው አለብን።

እሱ ላዋቀረው ቡድን?
አዎ! አውራው ላዋቀረው ቡድን። አንድን ድርጅት ወይንም መሪ ለሥልጣን የምናበቃው ብዙ አማራጮችን አገናዝበንና የዚህኛው ድርጅት ራዕይ ይጥመናል፤ ለኛም ላገራችንም ይበጃል ብለን ነውና የኛ ሀላፊነት እዚያ ላይ ማቆም አለበት። የመረጥነው የተሻለውን ፕሮግራም ብቻ ሳይሆን ፕሮግራሙን ለማስፈጸም በቂ ዝግጅትና ዕውቀት እንዲሁም ተአማኒነት አለው የምንለውን አውራ ጭምር ነው።

ልብ ብላችሁ ከሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ድርጅቶች ውስጥ እንዲሰፍን የፈቀድነው ያሠራር ባህል አውራን ሺባ ያደርጋል። ዕውቀቱም ልምዱም ታማኝነቱም አለህና ና ምራን ካልነው በኋላ ለመምራት የሚያስችለውን ሥልጣን እንነፍገዋለን። ከማያውቁትና ከማያውቃቸው ሰዎች ጋር ተጣመድና ውጤት አሳይ እንለዋለን። በዕውቀትም በባሕርይም በምንም እርሱን ከማይመስሉ ሰዎች ጋር አቆራኝተን “እየተግባባችሁ” ሥሩ እንለዋለን። የማኔጅመንትን ሳይንስ ያልተማረው ገበሬ እንኳ ትጉውን በሬ ከአባያ በሬ ጋር አያጣምድም። የተገራውን ካልተገራው ጋር አያሰማራም። አንዳንዴማ ደብዳቤ እንኳ ሳይቀር በጋራ እንዲረቀቅና በያንዳንዷ ቃል ላይ “የጋራ” ስምምነት እንዲኖር እንፈልጋለን። የጽሕፈት ቤት ሠራተኞች መቅጠር፤ መገምገምና አስፈላጊ መስሎ ሲታየውም ያስተዳደር ርምጃ መውሰድ የአውራው የማይገሰስ ሥልጣን መሆኑን እንኳ የማናውቅ አለን። በኔ ይሁንባችሁ ወገኖቼ! - ያወቀውና የተማረው በእንዲህ ዓይነቱ ኋላቀር ማሕበር ውስጥ ጥዋ አይጠጣም፤ አባልም መሪም ለመሆን አይጣደፍም። ለዚህ ሳይሆን ይቀራል በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ድርጅቶች ውስጥ በባለሙያ ፋንታ የተገኘው የተነሰነሰበት? - ባገር ቤትም በዳያስፖራውም ማለቴ ነው። ከለብ-ለብ አመራር ልንጠብቅ የምንችለው የኋልዮሺ ጉዞና እጅግ የቀናን እንደሁ ደግሞ ለብ-ለብ ውጤትን ነው።

ለዚህ ነው ፕሬዚደንትም እንበለው ሊቀመንበር፤ ጠቅላይ ሚኒስትርም እንበለው የድር ዳኛ፤ አብሮት የሚሠራውን ካቢኔ ወይንም ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመምረጥ መብት ሊኖረው ይገባል ብዬ የተነሳሁት። ይህ ሀሳብ እንደ ኮሶ የሚመራቸው “የጋራ አመራር” ደቀመዛሙርት እንዳሉ አልጠራጠርም። የቱንም ያህል ይምረራቸው እንጅ ትምህርትንና ሙያን በስሜትና በወገናዊነት ልናካክሳቸው እንደማንችል መቀበል አለባቸው።

በፖለቲካም በሌላውም መስክ ችኮ አቋም መያዝ በጎ አይደለምና እመሀል ላይ አስታራቂ መፍትሔ አግኝቻለሁ። እንዲህ ይሁን - አሠራሩን እስክንለማመደው ድረስ አውራው 51% የሚሆነውን ካቢኔ ወይንም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የመምረጥ ሥልጣን ይኑረው። ሳንውልና ሳናድር በሁሉም ዓይነት ድርጅቶች ውስጥ የአውራውን ሥልጣን (executive power) ብናጠናከር በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ ውጤታማነት ጣራ በጥሶ ይወጣል። ባለሙያውም ከየከተመበት ብቅ እያለ “እሺ ላገልግል” ይላል። የመጨረሻ ቤሳየን ሳልቆጥብ የምወራረድበት ጉዳይ ነው።

ታዲያ ይሄ አምባገነንነትን አይጋብዝም ወይ?
ፈጽሞ! አምባገነንነት በላያችን ላይ ይነግሥ ዘንድ የኛንም የማንንም ፈቃድ ጠይቆ አያውቅም። ለዚህ ከኢትዮጵያ የበለጠ ምስክር የለም። የምንመርጠው መሪ በኛና በርሱ መሀከል የተፈረመውን የራዕይና የፕሮግራም ሰነድ ተከትሎ ነው የሚሠራው። ይህን ለመከተሉ ማረጋገጫችን ደግሞ የተዘረጋው የቁጥጥርና የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት ነው። ለርሱ፤ ለሥራ አስፈጻሚውና ለጠቅላላ ጉባዔው አከፋፍለን የሰጠነው የሥራና የሥልጣን ድርሻ ነው። “አራተኛው መንግሥት” የሚባለው ነጻ ፕሬስም ፍቱን የማረጋገጫ መድሀኒታችን ነው።

የጋራ አመራር ጉዳይስ? የሰፊው ህዝብ ጉዳይስ?
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለበት አገር ሕዝብ ያገሩ ባለቤትም ነው የሥልጣን ቁንጮም ነው። መሪዎቹን የመምረጥና የመሻር ዕድል ባላገኘበት ሁኔታ ግን ሰፊው ሕዝብ የማንም ባለቤት የምንም ቁንጮ አይደለም። ሀቁን እንነጋገር ካልን ሰፊው ሕዝብ ከሚገለጽባቸው መለያዎች መሀከል መሀይምነት፤ ድህነት፤ ረሀብተኝነትና ኋላቀርነት ጥቂቶቹ ናቸው። ለተፈጥሮና ለመንግሥት አደጋ መጋለጥም የዋዛ አበሳዎቹ አይደሉም። ይህ ዕውነታ ዝንተ-ዓለም አብሮን መኖሩን እያወቅን ነው ሌኒናውያን “ታሪክ ሠሪው ሰፊው ሕዝብ ነው!” እና “የጋራ አመራር!” የሚሏቸውን ሴሰኛ መፈክሮች ኳኩለው ብቅ ያሉት። ታዲያ ይኼ በሕዝብ ጀርባ ላይ ፊጥ ለማለት እንዲጠቅማቸው ያመጡት እንጅ ሰፊው ሕዝብ አንዲት ሀባ ስልጣን ያየበት ጉዳይ አይደለም። ለነገሩ ሕዝብ ያልተማረ ከሆነ እንዴት ነው በጋራ መርቶ ውጤት የሚያስገኘው? እንዴትስ ነው ታሪክ ሊሠራ የሚቻለው? እስቲ እነዚህን መፈክሮች የሙጥኝ ብለው የነበሩ ሶሻሊስት አገሮችን ጤንነት አጠያይቁ። ሁሉም እንደከሰሩና አንዳዶቹም ብትንትናቸው እንደወጣ ትሰማላችሁ።

ትዝ ይላችሁ እንደሁ በ“ሰፊው ሕዝብ” እና በ“ጋራ አመራር” ዘፈን መደንቆር የጀመርነው ከ 1966 በኋላ ነበር። ጥቂት የማይባለው የሕብረተሰብ ክፍል በይሉኝታም ባድርባይነትም ባለማወቅም ተገፋፍቶ “አዎን ሰፊው ሕዝብ!” “አዎን የጋራ አመራር!” አለ። በግለሰብ የመፍጠርና የተነሳሽነት ኃይል ላይ ቀዝቃዛ ውኃ ቸለስንበት። ግላዊነት “እርኩስ-ወአርዮስ” ተብሎ እንዲያቀረቅርና እንዲሰደድ ተገፋ። ከግለሰብ ጋር ተፈጥሮዋዊ ቁርኝት ያለቸው ፋይዳዎች - ዕውቀት፤ ምጥቀት፤ ተነሳሺነት፤ ፈጣሪነትና ምሁራዊነት የንኡስ ከበርቴው ፀያፍ ባህርዮች ተብለው ተኮነኑ። በጥራት ፋንታ ብዛት፤ በዕውቀት ፋንታ ታማኝነትና ጎጥ፤ በሙግት ፋንታ የጅምላ ስምምነት ባህላችን ሆኑ። ከዚያን ዘመን ጀምሮ ነው መቅኖ ያጣ ሕዝብ የሆንነው ወገኖቼ።

የግለስቡ ጉዳይስ?
ባንጻሩ ደግሞ “ግለሰብ የችሎታም የፈጠራም የታሪክም ብቸኛ መንስኤ ነው” የሚሉ አገሮች አድገውና ተመንድገው እናያለን። የግለሰብ መብት መከበር የቡድንና ያገር ነፃነት መከበርን ያረጋግጣል ብለው ስለተማማሉ ዘንድሮም የብልጽግናና የመረጋጋት ባለቤት ናቸው። የግል
ንብረትንና የግለሰብ የፈጠራ ሥራ መከበርን የሕገ-መንግሥታቸው አውታር በማድረግ የተፈጥሮ ሃብታቸውን ባግባቡ እየፈለፈሉ ላገርና ለወገን ጥቅም አውለዋል። የጫካ መጨፍጨፍና በሣት የመጋየት አሳዛኝ ዕጣ አልደረሰባቸውም። አፈራቸው ተሟጦና ለዛውን አጥቶ ሕዝባቸው ለስደትና ለምጽዋት አልተዳረገም። እነዚህ አገሮች የሁሉንም ግለሰብ እድገትና የዕውቀት አድማስ በመገንባት ላይ ብቻ የተወሰኑ ሳይሆኑ ከዜጎች ውስጥ ልዩ ችሎታና ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች (ያገር ንብረቶች) እየመረጡ ተሰጥኦዋቸውን በሚመጥን ልዩ የ “ኤሊት” ትምህርት ቤት አስገብተው ይንከባከቧቸዋል - የነገው መሪዎችና የፈጠራ ሰዎች ከነርሱ መሀል ነው የሚገኙትና!

ማርክሲስቶች “ኤሊትዝም”ን ላፋቸው እንደማይወዷት ሁላችንም እናውቃለን። ይሁንና ልጆቻቸው ኤሊትና ያገር መሪ ይሆኑ ዘንድ በልዩ ትምህርት ቤት ለማስተማር የሚሽቀዳደሙት እነርሱው ናቸው። ሀርቫርድን፤ ስታንፈርድንና ፕሪንስተንን ለልጆቻቸው ሲቃዡ ነው የሚያድሩት። ልጆቻቸው የነዚህ ኤሊት ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቅ እንዲሆኑ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የሚሳሱለት ገንዘብ የለም። ከዚህ የበለጠ ሂፖፕክራሲ አለ?።

የኛውን አገር ታሪክ መለስ ብለን ብናይ ግለሰቡን የመኮትኮትና የማነጽ አስፈላጊነት ግንዛቤ ያገኘው ገና ትናንት በ1896 ዓ/ም ነው። ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የመጀመሪያውን የፈረንጅ ትምህርት ቤት ከግብጽ በመጡ ሁለት አስተማሪዎች ጀመሩና ይህን ጅምር በእጥፍ ድርብ ያፋጥኑት ገቡ (እኒህ መሪ 61 የዘመናዊነት መነሾ ፕሮጀክቶች እንደጀመሩ በብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን መጽሐፍ ላይ አንብቤ ተደንቄአለሁ)። አፄ ኃይለሥላሴም በምኒልክ ጅምር ላይ ብዙ ገነቡ። ከመደበኛ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ እንደ ጀኔራል ዊንጌት፤ ቅዱስ ዮሴፍና ሳንፎርድን የመሳሰሉ የኤሊት ትምህርት ቤቶች ተቋቋሙ። ከነዚህ ትምህርት ቤቶች ነው ብዙዎቹ መሪዎቻችን የወጡት - ቢያጠፉም ቢያለሙም።

ቀጥሎ የመጡት መንግሥታት ግን ጀኔቲክ መሠረታቸው ማርክሲስት ስለሆነ የግለሰቡ ተነሳሽነትና የልማት ሞተርነት ሊዋጥላቸው አልቻለም። መሬት የግል መሆኑ፤ ፍትሀዊ የንግድና የኢንዱትሪ መስክ መፈጠሩ ገበሬውንና ነጋዴውን ከጭብጣችን እንዲያፈተልክ ያደርጋል ብለው ስልሚሰጉ ፖሊሲዎቻቸው ፀረ-ግለሰብና ፀረ ውድድር ናቸው።

እነዚህ መንግሥታት በምሁሩ ላይ ያደረሱት በደልና አገር ጥሎላቸው እንዲወጣ ያካሄዱት ሴራ አንደኛው አንጀት-አቁሳይ ታሪካችን ነው። ምሁሩ ለማይፈልገኝና ለሚያንጓጥጠኝ ሕብረተሰብ ምንተዳዬ አለና መድረኩን ላላዋቂዎች አስረክቦ ኑሮውን ማሳመር ተያያዘ - ተሰደደም። የሚወደስበትና የሚከበርበት ዓለም ሲያገኝ ያን አዲስ ዓለም ዓለሜ ብሎ ተቀበለ። ባሁኑ ጊዜ የሀበሻ ባለሙያ ከሁዋይት ሀውስ እስከ ኮንግሬስ፤ ከወል-ስትሪት እስከ ሜይን-ስትሪት ከአካዴሚያ እስከ አምራችነት ተነስንሶበታል። ለተማረው ሕዝብ ፍልሰት (brain drain) ጥሩ ተምሳሌት ከፈለጋችሁ ሩቅ መሄድ አያስፈልጋችሁም ለማለት ነው።

ታዲያ ከየት እንጀምር?
የምንጀምረውማ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ከመቀየር ሊሆን ይገባል። ዴሞክራሲያዊ አሠራር ማለት “የጋራ አመራር” ማለት እንዳልሆነ እንቀበል። ሕብረተሰቡን ሳይሆን ግለሰቡን የመብትና የደሞክራሲ ሥርዓት መነሻም መድረሻም እናድርግ። ከስኬታማ ድርጅቶችና ሀገሮች በስተጀርባ ምንጊዜም አንፀባራቂ አውራዎች እንዳሉ አንዘንጋ። ባንድ ቤትና ባንድ ወቅት ሊኖር የሚችለው አንድ አውራ ብቻ ነውና ለመረጥነው አውራ በቂ ሥልጣን እንስጠው። እንንከባከበው። እንደንቦቹ ዙሪያውን ከበን ከሀሳየ-መሲሆች እንጠብቀው። እንዲፈታልን የምንጠይቀው ችግር ባንድ ጀንበር የሚሞከር አይደለምና ዋና መሥመሩን እስካልሳተ ድረስ ቢያዳልጠውም “አይዞህ አለንልህ!” እንበለው። አውራ የሌለው ምንም እንደማይኖረው እንወቅ!

ከሁለት ገጽ በላይ መጻፍ መንዛዛት ነው የሚለውን የራሴን ህግ ሰበርኩ ልበል?

kuchiye@gmail.com