Monday, May 05, 2008

"ችግሩ የማኔጅመንት ነው ወዳጄ! "

ኋላቀር አገር ብሎ የለም፤ በማኔጅመንት ያልታደለ እንጅ”
ይህ ጊዜ የማይሽረው አባባል ፒተር ድራከር የተባለ አሜሪካዊ የማኔጅመንት ጠቢብ
የተመራመረበት ነው። የፖለቲካም ሆነ የልማት ጥረታችን ክስረት ሰበቡ ምን ይሆን እያልኩ ሳሰላስል ነው ፒተር ድራከር ትዝ ያለኝ።

እስኪ ልብ እንበል። በተፈጥሮ ሀብት የተንበሸበሹ ሆነው ኋላቀርነት በሚያስከትለው መዘዝ
የጦርነት፤ የአፈና፤ የበሽታና የድንቁርና ሰለባ የሆኑ አገሮች ስንት ናቸው? በኛው ክፍለ ዓለም እንኳ ዛዬርን፤ አንጎላን፤ ናይጀሪያን፤ ሱዳንን መጥቀስ ይቻላል። ዘይት እንደጉድ
የሚገነፍልባቸውና አንዷን በርሜል በ$120 ዶላር የሚቸበችቡ እንደ ሳውዲ፤ ኩዌት፤ ኢራን፤ ኢራክና ቬነዙዌላ የመሳሰሉ አገሮች አሁንም የሚመደቡት እንደኋላ ቀር አገር ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የተፈጥሮ ሀብት ሳይኖራቸው ባዳበሩት የመኔጅመንት አቅምና በደረሱበት የልማት ደረጃ ብቻ ከበለጸጉ አገሮች የሚመደቡ እንደ ሆንግ-ኮንግ፤ ሲንጋፖር፤ ደቡብ-ኮርያና ታይዋን የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል። ቁምነገሩ ያለው እዚህ ላይ ነው። የኢንዱስትሪ፤ የአገልግሎትና የመልካም አስተዳደር መሠረቶች ያልዳበረበት አገር ቀጣይና የተረጋጋ ሕይወት ሊኖረው ስለማይችል እንደ በለጸገ አገር ሊቆጠር አይችልም። ስለሆነም የማኔጅመንት ባሕል ባልዳበረበት ሕብረተሰብ እድገትንም ሆነ አሸናፊነትን በርግጠኝነት መጠበቅ አይቻልም ማለት ነው። በፖለቲካው መስክም አሸናፊ ሆኖ ለመገኘት የዳበረ የማንኔጅመንት ሙያን ይጠይቃል።

ትምሕርት ያለ ሥራ ልምድ?
ይህን ካልን ደግሞ የኢንዱስትሪ፤ የአገልሎትና የመልካም አስተዳደር ዘርፎች መዳበር ከየት ይመነጫል የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ይሆናል። ወዲያውኑ በአእምሮአችን የሚመጣው“ትምሕርት”ቢሆን አያስገርምም። እዚህ ላይ ታዲያ አንድ የግንዛቤ ችግር አይጠፋም። ትምህርት የጽንሰ ሀሳቦች መሠረትና የመተንተን ችሎታን የሚያላብስ ምትክ-የለሺ እሴት ቢሆንም በሥራው ዓለም ካልተለበለበና የመታረቅ እድል ካልገጠመው ብዙ ፋይዳ አያስገኝም። ይህ ብቻ አይደለም። የተማረ ሰው እውቀቱን በማያቋርጥ የሥልጠና ፕሮግራምና በንባብ ካላደሰ ዱልዱም ቢላዋ የመሆን አሳዛኝ እድልም ይገጥመዋል። ለዚህ ነው በሰለጠነው ዓለም ዩኒቨርሲቲዎች፤ ኮርፖሬሽኖችና የመንግሥት አስተዳደር ዘርፎች ባለሙያዎችን እንደተውሶ እቃ የሚለዋወጧቸው። አሜሪካ የዓለማችን የማኔጅመንት እውቀት መናገሻና ተወዳዳሪ ያልተገኘላት የኤኮኖሚ ኃይል የሆነችውም በዚህ ፈር-ቀደደ ባህሏ ነው ።

አነሳሴ ለተደጋጋሚ የፖለቲካ ክስረታችን ስበቡ የማኔጅመንት አቅም አለማዳበራችን እንጅ
የርእዮት ወይንም የራእይ ማነስ አይደለም የሚለውን ለማመላከት ነውና ወደዚያ ከመሸጋገሬ በፊት ማኔጅመንት ለመሆኑ ምንድነው የሚለውን ልዳስ።

ማኔጅመንት ባጭሩ።
የማኔጅመንት ችሎታ ከተፈጥሮ የሚታደል ፀጋ የሚመስላቸው ቢኖሩም ሀቁ ይህ አይደለም። ማኔጅመንት በትምህርትና በስልጠና የሚገኙ ቴክኒካዊ፤ ቴክኖሎጅያዊና ስነ-አእምሮዋዊ ብቃቶችን፤ እንዲሁም በተግባር የተፈተነ ልምድን ይጠይቃል። በማኔጅመንት ሙያ ውስጥ የሚጠቃለሉት ተግባሮች ፈታኝና ውስብስብ ናቸው። ከነዚህ መሀከል፤ ሊደረስበት የሚችል እቅድ መንደፍን፤ ወደ እቅዱ የሚያደርሱ ስትራቴጂዎች ማውጣትን፤ የሰውና የማቴሪያል አቅም አሰባስቦ በብልሀት መጠቀምን፤ ችግሮች ሲከሰቱ ከስሜታዊነት ነጻ በሆነ መንገድ ተንትኖ ሲሆን በአሸናፊነት ካልሆነ ደግሞ ጉዳትን ባላበዛ መልኩ ችግሮቹን ፈትቶ ወደፊት መቀጥልን፤ ከተወዳዳሪዎች ጋር በጥቅም የሚያጋጭ ሁኔታ ከተፈጠረ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ ቀመር መፍታትን፤ በእቅድ ዘመን አንጓዎች ላይ ያፈጻጸም ምዘና እያካሄዱ የርምት ርምጃ መውሰድንና ከዛሬው የጥድፊያ ሥራ
ባሻገር እያማተሩ ሊከሰቱ የሚችሉ ፈተናዎችንና እድሎችን በቅድሚያ ተንብዮ ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግን ያጠቃልላል። ስለሆነም የኢንዱስትሪ፤ የአገልግሎትና የመልካም አስተዳደር መዳበር የማኔጅመንት ብቃት መዳበር ውጤት ነው ማለት ይቻላል። የፖለቲካ ውጤታማነትም እነደዚሁ። ከዚህ አንጻር በIትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ፓርቲዎችንና አገርን የመምራት እድል የገጠማቸውን ልሂቃን ስንመረምር ሁለት ጉድለቶች እናይባቸዋለን። አንድም የቴክኒክና የታክኖሎጅ ክህነት ያላገኙ ነበሩ፤ አንድም ደግሞ ትምህርቱ (ቴክኒክና ቴክኖሎጅው) ኖሯቸው በውነተኛው የተግባር ዓለም ውስጥ ድርጅት መርተው፤ ተለብልበውና በልምድ ዳብረው የወጡ አልነበሩም። ከ60ዎቹ ወዲህ የመጡትን ነጥለን ብናይ ደግሞ ወይንም ተማሪዎች፤ ወይንም አስተማሪዎች፤ ወይንም ደግሞ ወታደሮች ነበሩ።

ችግራችን ፈጽሞ የራዕይ እጥረት አይደለም!
ለሀገራችንና ለሕዝባችን ከምንመኘው Aንጻር ሲታይ ራእይ ገዶን አያውቅም። ከቅርብ ዘመን መሪዎቻችን ብንነሳ እንኳ ዮሐንስ፤ ቴዎድሮስ፤ ምኒልክ፤ ኃይለ ሥላሴና መግሥቱ ሀገራቸውን ከድህነት የማውጣትና ልUዋላዊነቷን የማስከበር ራእይ እንደነበራቸው አያከራክርም። የቱን ያህል አወዛጋቢ ቢሆንም መለስ ዜናዊም ባለ ራእይ ነኝ ባይ ነው። ታዲያ ራእይን በተግባር ለመተርጎም የሚያስችል የማኔጅመንትና የቴክኖሎጅ አቅም ስላልነበራቸው ነው ምኞታቸውም ልፋታቸውም ከመጨረሻው የድህነት እርከን ፈቀቅ እንኳ ያላደረገን። በኔ አመለካከት በዘመናችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሚታየው ችግርም ሆነ ለፍሬ አለመብቃታቸው ከማኔጅመንት ችሎታ ማነስ የመነጨ ነው። ለዚህ ይመስለኛል ለፍትህና ለዴሞክራሲ ስርጸት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ የሆኑ ወገኖቻችን የሚለካ መርሀ-ግብር አውጥተው ከመንቀሳቀስ ይልቅ ማንም አዋቂ መስሎ ሊታይ በሚችልበት ርእዮታዊ ክርክር ላይ እድሜያቸውን የሚፈጁት። የግሪክ ፈላስፋዎች“ፈረስ ስንት ጥርስ አለው?” በሚል ርእስ እስኪነጋ ይከራከሩ ነበር ይባላል። ወጣ ብለው የታሰሩ ፈረሶቻቸውን ጥርስ ቢቆጥሩ መልሱን በሁለት ደቂቃ ውስጥ ሊያገኙት ሲችሉ።

ዕቅድ! ዕቅድ! ዕሁንም ዕቅድ!
የፖለቲካ ፓርቲዎች የዛሬውን የፖለቲካ ሁኔታ በተጨባጭ ገምግመው፤ የወደፊቱን ተንብየው፤ ከዚህ ተነስተን እዚያ መድረስ እንፈልጋለን ብለው ያወጡት የአምስትና የአስር ዓመት ዕቅድ ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። የረጅም ጊዜ እቅድና የስትራቴጅ ትልም አላቸው ብንል እንኳ ዕቅዱን በስትራቴጅ ትልሙ መሠረት ለማስፈጸም የሚያስችል በቂ የባለሙያና የማቴሪያል ኃይል አሰባስበው ባንድ ልብና ባንድ መንፈስ ብቻ ሲተጉና ከዳር ሲያደርሱ አናይም። ፓርቲዎቹም ልሂቃኑም ከየሱባኤያቸው ብቅ የሚሉት ብሄራዊ ቀውስ ሲከሰት፤ ወይንም የሕዝብ ስሜት ተነክቶ ቁጣና ቁጭት ሲገኑ ብቻ ነው። ድፍረት አይሁንብኝና ይህ ባሕርይ የሚያስመድበው ከሠለጠነው ወገን ሳይሆን በደመ-ነፍስ ከሚመራው ከወደ አራዊቱ ነው። ለምሳሌ ያህል፤ የ1953 1966 እና የ1980 የፖለቲካ አጋጣሚዎች በተከሰቱ ጊዜ ፓርቲዎቻችን የተያዙት ሳይደራጁ፤ ወይንም
በረንጆቹ አባባል ቁምጣቸውን ዝቅ እንዳደረጉ ነው።

“የምትሄድበትን ካላወቅህ ሁሉም መንገድ እዚያ ያደርስሀል”ይላል ዮጊ ቤራ የተባለው አሜሪካዊ የቤዝቦል ባለታሪክ...ከማታውቀው መንደር ማለቱ ነው። ልንደርስ የምንፈልግበትን ግብ ወስነን፤ የመንፈስና የማቴሪያል አቅማችንን ለዚህና ለዚህ ብቻ ዳርገን መንቀሳቀስ ካልጀመርን አድሮ ጭቃ የመሆናችን እድል የጎላ ነው።

ከየት እንጀምር?
በኤኮኖሚና በማሕበራዊ ቀውስ፤ በወታደራዊ ጣልቃገብነት፤ በሙስና፤ በዘረኝነትና በመብት ረገጣ የድጋፍ መሠረት ያጣው የIሕአዴግ አገዛዝ ብዙ እድሜ ሊኖረው እንደማይችል እየታወቀ የሚከሰተውን ያመራር ኦና ለመሙላት ፓርቲዎች የቱን ያህል ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል ብለን መጠየቁ ፍጹም አግባብነት አለው። ተዘጋጅተናል ወይንም እየተዘጋጀን ነው የሚሉን ቢሆን ጥንስሱን አሳዩን ብለን መሞገት መብታችን ይመስለኛል። ስንፍና በ “ምሥጢራዊነት”እያሳበበ እንዲሸነግለን መፍቀድ የለብንም።

የፓርቲዎቹ የአምስት እና የአስር ዓመት ዕቅድ ቢያንስ የሚከተሉትን አካቶ ማየት እንፈልጋለን። ዘመናዊ መዋቅር፤ ዕቅዱ ላይ የሚያዳርስ የስትራቴጅ መርሀ-ግብር፤ በተወሰኑ ኢላማዎች ላይ ያተኮረ የማስተማርና የመቀስቀስ ፕሮግራም፤ አሃዛዊ የአባላትና የደጋፊዎች ምልመላ፤ በተወሰኑ ግኝቶች ላይ ያነጣጠረ የሎቢ፤ የዲፕሎማሲና የትብብር ሥራ፤ በፕላን ዘመኑ አንጓዎች ላይ የሚደረግ ያፈጻጸም ግምገማ፤ በግምገማው ላይ የተመሠረተ የድክመቶች ማረሚያ ሥርዓትና የመሳሰሉት።

ከላይ የተዘረዘሩት ተግባሮች የማያከራክሩና “ደ!” የሚያሰኙ ይመስላሉ እንጅ ይህ ነው የማይባል ዕውቀትና ልምድ፤ የባላሙያዎች ተሳትፎ፤ የገንዘብና የማቴሪያል ኃይል፤ የማስተባበርና የስምምነት መፍጠር ችሎታን የሚጠይቁ ናቸው። በተሳካላቸውና ገና በሚንደፋደፉ፤ በጫጩና በሚመነደጉ ፓርቲዎች መሀከል ያለው ልዩነት ይህ የብቃት ደረጃ ብቻ ነው። ሌላ ምስጢር የለውም።

በፕላን ያልተመራ የደመነፍስ እንቅስቃሴ ባስቸኳይ ሊቆምና ወደተረጋጋና በመልካም
የማኔጅመንት ሥርዓት ወደሚመራ ዘመን መሸጋገራችን ወሳኝነት አለው። በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ፤ ፍትሕና መልካም አስተዳደር የማምጣትን ክቡር ሥራ የ “ፖለቲከኞች” ድርሻ
አድርገን መቁጠር ትልቅ ስህተት ነው። ትግሉ ይበልጥ የሚጠይቀው የፖለቲካ ከያኒዎችን
መደራረብ ሳይሆን በማኔጅመንት ሙያ፤ በቴክኒክና በቴክኖሎጂ መስክ የተካኑና የተፈተኑ
ዜጎችን ጭምር ስለሆነ ለነዚህ የሙያ ዘርፎች የላቀ ክብርና ቦታ ልንሰጥ ይገባል። ባለሙያዎችም ለፖለቲካ ሰዎች ያላቸውን ምጸትና ጥርጣሬ አስወግደው ወገናችን የዴሞክራሲ፤ የፍትህና የመልካም አስተዳደር ባለቤት እንዲሆን በሚደረግ ክቡር እንቅስቃሴ ውስጥ አስተዋጽኦ ለማድረግ ሸሚዛቸውን መጠቅለል አለባቸው።
kuchiye@gmail.com