Thursday, February 23, 2012

በፍቅር ታድለሀል!





“ለፍቅር አልታደልኩም” አትበል
ፍቅርን በውል ሳትፈልጋት
ሳታጠና ወጓን
ሳትካነው ቋንቋዋን::
ፍቅር ትገብራለች አቡሻክሯን ለቆጠረ
ሰምና ወርቋን ተክኖ ዜማ ወረቧን ላሳመረ::
ፍቅር ጽጌረዳ ናት የላመ መሬት የምትወድ
የተቡ ጣቶች ስታገኝ የምትፈወስ የምታድግ፤
ጣይ ሙቀት ይመቻታል
አረም ያሰጨንቃታል፤
ነጎድጓድ ያስፈራታል
ውዳሴ ያከንፋታል፤
ስለዚህ እወቅበት ወጉን
ተማር ውስጠ-ነገሩን
ደህና አርገህ አጥና አቋቋሙን፤
ውደድ የምትወዳትን
ውድ-ድ-ድ-ድድ አድርጋት፤
ከራስ እሰከግር ጥፍሯ
በቀናነትህ አርሳት፤
ሥራ የፍቅር መቅደስህን
ንሴብሆ! በል ሕይወትህን፤

ለመልካም አንደበት ለበጎ ስብእና
እጇን መስጠቷ አይቀር ፍቅር ገር ናትና።

ኩችዬ (የካቲት 2004)