Thursday, November 05, 2009


ከሳጥን ውጭ ማሰብ አይከፋም!
(ስለ ሀይሉ፤ ኢህአዴግ፤ ፈረንጆቹና ብርቱካን)

ብርድ ልብስ ውስጥ እንደተጀበንኩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ መፍታት ሲሳነኝ የቡና ተርቲበኛ ወዳጄን “ካሪቡ” እንደምቀጥረው አምና አካባቢ ያጫወትኳችሁ መሰለኝ። እጣኑ ይጐድል እንደሁ እንጅ የካሪቡ ቡናና የቤቱ ጌጥ (ፌንክ-ሹዌ ይሉታል ቻይናዎች) ከራማ ያስታርቃል። ታዲያ ይሄ ወዳጄ አንገቱን ከብርድ ልብስ ውስጥ ብቅ አርጎ መወያየትን አይፈራም። ጥልቅ አሳቢነቱን ብቻ ሳይሆን ወዛም ጨዋታውንም እናፍቀዋለሁ። እንዲህ ያለ ወዳጅ አያሳጣችሁ አቦ!

“እናም ሀይሉ ሻውል 2010 ምርጫ ውስጥ ለመግባት መወሰኑ ከምን መጣ? በእሥር የተንገላታበት የቅንጅት ባለ ስምንት ነጥብ ቅድመ ሁኔታስ ምን ጅብ በላው? ከትናንት በስቲያ የብርቱካን መፈታት ቅድመ ሁኔታ ነው አላለም ነበር ወይ? በርግጥ ሀብቱንና ንብረቱን ካደጋ ለመጠበቅ ሲል ያደረገው ሰጥቶ-መቀበል ነው? በ2005 ምርጫ ያሳዘናቸውን ደጋፊዎቹን እንደገና ማሰባሰብ እችላለሁ ቢል የለየለት እብደት አይደለም ወይ?” እነዚህንና ሌሎችንም ጥያቄዎች ወዳጄ ላይ ያራገፍሁት እንደመትረዬስ ነበር።

በንዲህ ያለ ስሜታዊነት ጨዋታ በጀመርኩ ቁጥር ምንጊዜም ዓይኑ ወደጣራው እጁ ወደ ቡናው ስኒ ነው የሚያመራው። በርጋታ ፉት ብሎ እስኪያጣጥም ድረስ የኔ ስሜት ሳይወድ-በግዱ እንደሚበርድ ያውቃል። ሰው የዚህን ያህል ውስጣችሁን ሲያነብ እህ! አትሉም? ቀጥልኩ ደግሞ ስለምርጫው - “የኢሕአዴግ ስሌት ምን ይመስልሀል? ምን ያህል ያገር ውስጥና የውጭ መንግሥታት ተጽዕኖ አለበት? ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም ያለው አቅምስ? የኦባማስ አዲስ ፖሊሲ? ኢዩስ? የብርቱካንስ ጉዳይ? መድረክ ምርጫው ውስጥ የሚሳተፍ ይመስልሀል?....” ትንፋሼ መቆራረጥ ሲጀምር ራሴን ታዝብሁና እኔም እጄን ወደቡናው ስኒ ላክሁ።

ጥቂት ሴኮንዶች በፀጥታ ካለፉ በኋላ ጨዋታችን በተረጋጋ ሁኔታ መቀጣጠል ጀመረ። ሰው የሚያዘውትረውን ጎዳና ትተን በማይጓዝበት መስመር ማሰብና መመርመርን ቀጠልን። ጨዋታችንን ከነሙሉ ለዛው የማቅረብ ክህሎት ቢኖረኝ ምንኛ ደስ ባለኝ። ለዛሬው ግን ፈረንጆቹ እንደሚሉት ከሣጥኑ ወጣ ብለን (እኔ ከብርድ ልብሱ ያልኩት መሆኑ ነው) ለማሰብ ያደረግነውን ሙከራ አቃምሳችኋለሁ። “ይሄን መቼ አጣነው?” ለምትሉ አዋቂዎች ይቅርታ፤ የሚጥማችሁ ከተገኛችሁ ደግሞ መልካም።

የሀይሉ ሻውል ጉዳይ!
ሀይሉ ሻውል ሰንበት ያለ ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን የተዋጣለት ነጋዴም ነውና ችሎታውን አኮስሶ ማየት የተዛባ ድምዳሜ ላይ ይጥላል ብለን እንሰጋን። በቃለ-ምልልስ ወቅት አንገት ከሚያስደፋው ሀይሉ ሻውል በስተጀርባ ሌላ ሀይሉ መኖሩን ታሳቢ ማድረግ በፖለቲካ ሳይንስ ሕግም የተደገፈ ነውና በዚህኛው ወገን መሳሳትን መረጥን። ይህን መነሻ አድርገን ነው የሀይሉን ድርጊት በለሆሳሱ የመረመርነው።

ሀይሉ እንደማንኛውም ፖለቲከኛ ለሥልጣን የተሰለፈ ሰው ነው። ችግሩ ግን ዕድሜው የገፋው ሀይሉና የዕድሜ ወስን የማታውቀዋ ሥልጣን በተለያየ ፍጥነት መሮጣቸው ላይ ሆነ። “ከህልፈቴ በፊት ታሪክ ገበታ ላይ ስሜን መቅረጽ አለብኝ” ብሎ ከተነሳ ማን ሊያቆመው ይችላል? ጥያቄው ታሪኩ የሚጻፍበት ርዕስና በየትኛው ገጽ ላይ ይሆናል የሚለው ብቻ ይሆናል። ሀይሉ የፖለቲካ ካርታዎች እንዳሉትም እንዘንጋ። የሀይሉ ስም ከመላ አማራ፤ መላ ኢትዮጵያና ከቅንጅት ጋር በተያያዥነት ሲነሳ ኖሯል። የስም ታዋቂነት ደግሞ በፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ንብረት ነውና በተለይ በገጠሩ የአማራ ክልል ድጋፍ ሊያገኝ የሚችል ይመስለናል። አንዳንዶች እንደሚሉት ስሙ ጎድፎ ቢሆን እንኳ በባለሙያ የሕዝብ ግንኙነት ዘመቻና በገንዘብ ኃይል ሊታደስ የሚችል ነው። “የህዝብ ማስታወስ ችሎታ አፍታዊ ነው! ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ! ስለትናንቱ አትንገረኝ ዛሬ ምን አደርግክህልኝ!” የሚሏቸውን የፖለቲካ ብሂሎች ታውቁ የለም? ከዚህም ሌላ የሀይሉ ፓርቲ ባንዳንድ ክልሎች ውስጥ ማልዶ ሥራ መጀመሩ በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች የወደፊት ይዞታ ላይ ተጽዕኖ አይኖረውም ማለትም አይቻልም።

ከሳጥን ውጭ ማሰባችን ካልቀረ ዘንድ በሀይሉ ጭንቅላት ውስጥ ሊመላለሱ የሚችሉ ሀሳቦችንም ቃኝተናል። “ኢሕአዴግ ለተወሰኑ ዓመታታ ሥልጣን ላይ መቆየቱ የማይቀር ከሆነ ሜዳውን ወለል አርገን መልቀቅ የበለጠ ጥፋት እንዲያደርስ የመፍቀድ ያህል ነው፤ ባለው የፖለቲካ ምሕዳር ውስጥም ኢሕአዴግን ማጋለጥ ምህዳሩንም እንዲሰፋ መግፋት ይቻላል፤ በፖለቲካ ጠርዝ ላይ ለረጅም ጊዜ መቆዬት መረሳትን ያመጣል ከበሬታንም እየቀነሰ ይሄዳል ወዘተ” ብሎ አስቦም ሊሆን እንደሚችል ገመትን። ከ 2005 ምርጫ ወዲህ ተቃዋሚው ወገን በፖለቲካ ጠርዝ ላይ አልሰፈረም ማለት ይቻላል?

ሌላም ከበድ ያለ ነገር አይጠፋ። ኢሕአዴግ፤ አሜሪካና የአውሮፓ ማሕበር “መኢአድ”ን እሹሩሩ ሲሉ ለመክረማቸው አያሌ ማስረጃዎች አሉ። ሀይሉ በድርድሩ ውስጥ መቆየቱ መድረክ አባላት ላይ ሥነ-ልቦናዊ ጫና ነበረው። መንግሥትና አምባሳደሮቹ ሀይሉን በኪሳቸው አርገው ነው መድረክን ሲጫኑ የከረሙት። በመጨረሻም ሀይሉ ፊርማውን በነጠብጣቡ መሥመር ላይ ባስቀመጠ ዕለት ተጨማሪ ተጽዕኖ ተፈጥሯል ባይ ነን። ያቶ መለስና የበረከት ስምኦን ደስታ ከዚያ የመነጨ ይመስለናል።

ታዲያ ሀይሉ ይህንን ሁሉ ውለታ የዋለው በነፃ ይመስላችኋል? ፈጽሞ! ከኢሕአዴግም ከፈረንጆቹም ተገቢውን ካሣ ለማግኘቱ አንጠራጠርም። አለያማ ርባና ያለው ፓለቲከኛም ጥሩ ነጋዴም አይደለም። ቢያንስ ቢያንስ ጥሩ የሚዲያ ጊዜ፤ የተመቻቼ የመንቀሳቀሻ ምህዳርና የገንዘብ ዳረጎት ያገኛል። የመልካም ተቃዋሚ ምሣሌ ለማድረግ ሲሉም በፓርላማና በያደባባዩ የክብር ቦታ ይሰጡታል። በውጭው ዓለም ደግሞ አሜሪካና አውሮፓ ለታላላቅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ ዲፕሎማቲክ ኢሚውኒቲና የክብር አቀባባል ቃል ገብተውለት ይሆናል። እነዚህ ነገሮች የትኛውንም ፖለቲከኛና የፖለቲካ ድርጅት ሲጎዱ አይተን አናውቅም። የዘረዘርናቸው ታሳቢዎች ዕውነት ከሆኑ ሀይሉ የፖለቲካ “ሃርድ-ቦል” ተጫውቷል ማለት እንችላለን።

ኢሕአዴግን በሚመለከት….
ከዕውነተኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሀከል ዳጎስ-ዳጎስ ያሉት በ2010 ምርጫ ካልተሳተፉ ለ ኢሕአዴግ ኪሣራ ነው። ባገር ውስጥም በውጭው ዓለምም መሳለቂያ እንደሚሆን ያውቀዋል። አዲሱ የኦባማ መንግሥት ደግሞ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለቀቅ እንዲያደርግ አምባሳደር ባለመሰየምና ከፍተኛ ባላሥልጣኖቹን በመላክ ጫና እያሳደረበት ነው። አውሮፓውያን ለኢሕአዴግ ጥፋቶች ይቅርታ ማፈላለግ ሰልችቷቸዋል። ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ እምባ-ጠባቂ ድርጅቶች ይህን መንግሥት አሁን ከሚገኝበት ጭራ ደረጃ ወዴት ዝቅ እንደሚያደርጉት ግራ ሳይጋቡ አልቀሩም።

ከላይ የተዘረዘሩትና ሌሎችም ችግሮች ናቸው ኢሕአዴግን ወደ ድርድር ያመጡት። የሀይሉ ሻውል ፊርማ ምርጫው በጽኑ የሚፈልገውን “ሌጂቲመሲ” ባይሰጠውም ላፍሪካ ብዙ ትዕግሥት በሌላቸው ምዕራባውያን ዘንድ “የሚያበረታታ ጅምር” ተብሎ የሚታለፍ ዓይነት ሆኖ ይታየናል። ይሁን እንጅ ምርጫው እርባና ያለው ሌጅቲመሲ የሚያገኘው የቅንጅት ወራሺ የሆነው አንድነት ፓርቲ ወይንም በቅርቡ የተመሠረተው መድረክ ሲሳተፉ ብቻ እንደሆነ አይስቱትም። በዚህም የተነሳ ከአንድነትና ከመድረክ ጋር ውይይት አላቋረጡም የሚል ስሜት አድሮብናል።

በዚህ በ2010 ምርጫ ድርድርና ቻቻታ ውስጥ የተደበቀውንም የኢሕአዴግ ግኝት አንርሳ። “መኢአድ” በሙሉ ኃይል መንቀሳቀስ የሚጀምረው በ “ብአዴን” ኪሣራ ነው። ለዚህ ነው መለስ ሰፊ የሕዝብ መሠረት ያለውንና የሚፈራውን ያማራውን ክልል ለሁለት በመሰንጠቁ ደስተኛ ሊሆን የሚችለው። ምስኪን ብአዴን!

በየትኛውም ወገን እያገላበጥን ብናዬው ከሰሞኑ ሆያሆዬ እንደ ኢሕአዴግ የተጠቀመ የለም። ስለሆነም በምርጫው ስሞን ሚዲያውን ከፈት፤ ወከባውን ቀነስ፤ እሥረኛውን ለቀቅ ... በማድረግ ጥሩ ልጅ መስሎ ቢታይ ልንገረም አይገባም። ያን ካደረገ የርዳታውም የምኑም ቧንቧ እንደማይዘጋበት ያውቃል።

አሜሪካንና አውሮፓ ሕብረትን ደግሞ እንዳስ?
የኦባማ መንግሥት የውጭ ፖሊሲ ያገሩን ብሔራዊ ጥቅም ተከትሎ እንደሚሄድና ከቀድሞው ብዙም ሊለይ እንደማይችል ባለፈው የተስማማን ይመስለኛል። ይህን በሚመለከት “በርግጥ ኢትዮጵያ ላይ ሴራ አለ?” በሚል አምና አካባቢ ያቀለምኳትን እንድታነቡ እጋብዛችኋለሁ። http://kuchiye.blogspot.com/2008_07_01_archive.ht

ዘመዶች! ፈረንጆቹ ያፍሪካ ቀንድ የውጭ ፖሊሲያቸውን የሚያጠነጥኑት ሁለት እንዝርቶች ላይ መሆኑን አትዘንጉ - እርግጥ ዘይት መሳይ ቢኖረን ሦስተኛ እንዝርታቸውን ከማውጣት ወደኋላ አይሉም። አንደኛው እንዝርት ባፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጥ እልቂት የሚያስከትል የፖለቲካ ቀውስ አለመኖሩን የሚያረጋገጥ ሲሆን ሁለተኛው እንዝርት ደግሞ ሺብርተኞች ባካባቢው አስቀያሚ ድራቸውን እንዳያደሩ የሚከላከል ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ሁነኛ አማራጭ ኃይል እስካላገኙ ድረስ መለስ ላይ የሚቻላቸውን ያህል ተጽዕኖ እያደረጉና የሚያገኙትን ያህል የፖለቲካ እንጎቻ እየተቀበሉ ከመኖር የተሻለ አማራጭ የላቸውም። መለስ በሁለት ያማራ ድርጅቶች ቅልልቦሺ ለመጫወት እንደታደለው ሁሉ እነርሱም በኢሕአዴግና በሌላ አማራጭ ፓርቲ ቅልልቦሺ መጫወትን ይፈልጋሉ። ይሄ ነዋ የፖለቲካ ሳይንሱ።

የብርቱካን ጉዳይ!
ከወዳጄ ጋር የምናደርገው ወግ ከሳጥን ውጭ በማሰብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን እያወቅን እንኳ የብርቱካን ተራ ሲደርስ ስሜታችን እንደመጋል አለ። ብርቱካን የምን ተምሳሌት እንደሆነች እንኳንስ ያበሻ ሰው ተክሉና አራዊቱም ያውቃልና በዝርዝር ትችት አናሰለቻችሁም። መንግስታት ሳይቀሩ የዚችን ሠላማዊ ትግል አራማጅ መሀረብ ማውለብለብ ጀምረዋል።

ታዲያ የጥያቄዎችም ጥያቄ የሆነብን “ይሄ ኢሕአዴግ ብርቱካንን በማሠር ምን የፖለቲካ ትርፍ አገኘ?” የሚለው ሆነ። ብርቱካንን የዴሞክራሲ ትግሉ ሰንደቅና ማዕከል ነው ያደረጋት። ብርቱካንን ባልረባ ሰበብ ማሠሩ ኢሕአዴግን በቀለኛና እብሪተኛ መንግሥት የሚል ስም ነው ያከናነበው። መቀራረብ ተስኖት የነበረውን የተቃዋሚው ጎራ ነው እንዲሰባሰብ ምክንያት የሆነው። ባጭሩ ትልቅ የፖለቲካ ቡቡ ነው የሠራው!

ታዲያ 2010 ምርጫን አስመልክቶ የብርቱካን መፈታት ለሁሉም ነገር ቅድመ ሁኔታ ሆኖ መቅረቡ ማንንም ሊያስደንቅ አይገባ። ሕዝቡም፤ ፖለቲካ ፓርቲዎቹም፤ የውጭ መንግሥታትም ብርቱካን እንድትፈታ ይፈልጋሉ። ጥቂት የማይባል የኢሕአዴግ ደጋፊ እንኳ የብርቱካን መታሠር የፖለቲካ ፋይዳ እንደሌለው ከመነሻው ጀምሮ ይከራከር እንደነበር እናውቃለን። በዚህ ሁሉ የተነሳ ነው ዲፕሎማቲክ ሕብረተሰቡ የብርቱን ጉዳይ እኋለኛው ምድጃ ላይ ሊጥድ ያልቻለው። ለዚህም ነው መድረክ፤ ኢሕአዴግና የውጭ መንግሥታት ተወካዮች ባደረጓቸው ስብሰባዎች ላይ ሁሉ አቢይ መነጋገሪያ የሆነችው።

ኢሕአዴግ ብርቱካንን ይፈታል። ስንብቶም ቢሆን የተጫወተው ቁማር እርሱን እንዳልጠቀመው ገብቶታል። የምትፈታበትን አጋጣሚ ግን ቸርና ይቅርታ አድራጊ መስሎ የሚታይበት ያደርገዋል። ሀይሉ ሻውልና ዲፕሎማቶቹም የኛ ልፋት ፍሬ ሰጠ ለማለት ይሺቀዳደማሉ፤ አንዱ የሌላውን ጀርባ ቸብ-ቸብ የሚያደርግበት ዘመንም ይሆናል።

ከምርጫው በፊት ብርቱካንን ለመፍታት ኢሕአዴግ ወኔው ይኑረው አይኑረው የሚታይ ነገር ነው።

“Thinking out of the box”
The case of Hailu, EPRDF, the Ferenjies and Bertukan
kuchiye@gmail.com

ማሳሰቢያ
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ “የተከበሩ፤ አቶ፤ ወይዘሮ፤ ኢንጅነር... ወዘተ” የሚሉትን ቅጽሎች ያልተጠቀምሁት ለሰዎቹ ከበሬታ ሳይኖረኝ ቀርቶ አይደለም። በፖለቲካ ሥነጽሁፍ የተለመደ አሠራር ስለሆነ ነው። “ኢንጅነር እከሌ” የሚሉት መጠሪያ ካለ “አካውንታንት እከሌ” “ኤኮኖሚስት እከሌ” ስንል ልንኖር ነውና እባካችሁ ይህን አጉል ባህል እንተው። ከየት እንደመጣ የሚያስረዳኝ አለ?”