Friday, November 14, 2014

“የተቆለፈበት ቁልፍ” (439 ገጽ) - ቅኝት በኩችዬ

 

ደራሲ፤ ምሕረት ደበበ ገ/ጻዲቅ (ዶ/ር) - ሮሆቦት አታሚዎች፤ አዲስ አበባ፤ መጋቢት 2005

አገር ቤቱ ዳያስፖራ፤ ዳያስፖራው ደግሞ አገር ቤት እየሆነ በመጣበት በዚህ ህልሙም፤ ቅዠቱም፤ ባህሉም፤ ኑሮውም ተወራራሺ በሆነበት ዘመን የሥነ ጥበብ ሰዎች አስጎምዥ የትረካ አውድማ እንደተቸሩ ሳውቅ ሰንብቻለሁ።

   የምሕረት ደበበ ልቦለድ ታሪክ ስድሰት ሺህ ማይል አራርቋቸው በሚኖሩ ያበሻ ሕበረተስቦች ሁለንተናዊ ባሕርይና ዕጣ-ፈንታ ላይ የተመሠረተ ነው። የደራሲው አንድ እግር አሜሪካ፤ ሌላኛው እግር ደግሞ ኢትዮጵያ መሆን የሁለቱንም ሕብረተሰቦች ውጫዊና ሥነ-ዓዕምሮዋዊ ባሕርይ፤ እንዲሁም የየቤቱን  ውሎና ከራሞ በቅርብ ለማስተዋል ዕድል እንደሰጠው ከትርካዎቹ ማስተዋል ይቻላል። ሁለቱም ሕብረተሰቦች ውስጥ እየተከሰተ ያለው ፈጣንና አንዳንዴም አስፈሪ የሆነ ማሕበራዊ ለውጥ የብዙ ደራሲያንን እንዲሁም በየሙያ ዘርፉ ያሉ ጠቢባንን የሰላ አእምሮና  ብዕር የሚጋብዝ ነውና እንደ ምሕረት ደበበ ያሉ ብዕር ሲያነሱ ደስ ይላል።

   “የተቆለፈበት ቁልፍ” በኮሜርሻልና በሊተራሪ ልቦለድ የትርካ እርካቦች ላይ የተንፈራጠጠ ነው። ይህ የትረካ ምርጫ አንባቢን ከዳር እሰከዳር ይዞ በመዝለቅ ረገድ አስቸጋሪ ቢሆንም ደበበ ፈተናውን በሚገባ  ተወጥቶታል። ልብ-ሰቃይ ሴራዎቹ ገጾችን ቶሎ ቶሎ ያስገለብጣሉ። እንደ መላኩ፤ አቶ ኦላናና ሰሊ ዓይነት ገጸ-ባሕርያት ደግሞ ሀገራዊ፤ ሕብረተስባዊና ግላዊ ባህሪዎችን የሚተነትኑበት አንጎል ጥልቅና ፊሎሶፊያዊ ስለሆነ አንዳንዴ ትረካው ቢረግብም የዐእምሮ ምግብ ነው። ከንባብ የሚፈለገው እሴት እንደየሰው ዝንባሌ፤ ዕድሜና የትምህርት ደረጃ ቢለያይም እንደኔ ዓይነቱ ልብ ሰቃዮቹንም ጥልቅ ትንታኔዎቹንም ስለሚሻ በመጽሐፉ ይረካል።

   የመጽሐፉ ጭብጥ በዘመናችን ሕብረተሰብ አመለካከቶች፤ የኑሮ ምርጫዎችና ሥነ-ዓዕምሮዋዊ ለውጦች ላይ ያተኮረ ነው - አገር ውስጥም ውጭም ባለነው ላይ። ገጸ-ባህርያቱ ተአማኒነትና መልካም ስብጥርም አላቸው።   

   አሜሪካ ተሻግራ ሃብታም ለመሆን ባላት ምኞት የድሜ አቻዋ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ያገባችው ስንክሳር  አገር ቤት ግድግዳ አስደግፋ የተወችውን የወጣትነት ፍቅረኛዋን (የመላኩን) ልብ መልሳ ለማሸነፍ የምታደርገው ሴራ ውስብስብና እጅግ መሠሪነት የበዛበት ሰለሆነ ስንክሳርን በጣሙን ትጠሏታላችሁ፤ ትፈሯታላቸሁ፤ ልታንቋትም ይከጅላችሁ ይሆናል። መጨረሻ ላይ ደግሞ እርሷ ራሷ በደረተችው ተንኮል ተጠልፋ ዙሪያ ዓለሟ እየፈራረሰባት ስታዩ “ሰው ተፀፅቶ ከልብ የሚወደውን ቢሻ ይህን ያህል ፍርድ ሊቀበል ይገባዋል ወይ?” የምትሉም አትጠፉ።

  መላኩ ባንዲት ሴትዮ ትሩፋት ምንጥ ካለ ድህነት የተረፈና በውጭ  አገር ጭምር ትምህርቱን ተከታትሎ “ባገሬ    

ውስጥ ለውጥ ማምጣት እችላለሁ” ብሎ በምግባረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ ሀቀኛ ጥረት የሚያደርግ ሰው ነው። በመልካም ባህርዩም፤ በጥልቅ አስተሳሰቡም፤ በፍቅረኛው በስንክሳር በመገፋቱም ለመላኩ ስስ ልብ ይኖራችሗል።

አብሮ ያላደጋቸውን ዘመዶቹን ፈልጎ በማግኝት ከድህነት መቀመቅ ለማውጣት ያደረገውን ጥረትና ይህ ዘመቻው ፍሬ እንዲያገኝ መሣሪያ የሆነችውን ግን በትምህርት ያልገፋችውን ያክስቱን ልጅ በጣሙን ትወዷታላቸሁ።    

   የመላኩ ጓደኛ ማርቆስም እንዲሁ ከውጭ የተመለሰና አገሪቱ ውስጥ በተንሰራፋው ጉቦኝነት ሳይጠለፍ በንግዱ ዓለም ውስጥ የተሳካለት መልካም ሰው ስለሆነ እሱንም ትወዱታላችሁ። ባንጻሩ ደግሞ የማርቆስ ወንድሞች “ቶሎ ሃብታም ለመሆን ጉበኞችን ማሰተናገድ ግድ የሚል ከሆነ የኸው ሊፈጸም ይገባል” የሚሉና ሗላም ስግብግብነታቸው ያስጠለፋቸው ስለሆነ እሰይው ያስብላችሗል። ሁለቱንም ዓይነት ሰዎች እነደምታውቁ ወይንም የሚያውቁ እንደምታውቁ አልጠራጠርም።

   ደራሲ ምሕረት ደበበ የሥነ-አዕምሮ  ጠበብት ስለሆነ በገጸ-ባሕርያቱ ውይይት ውስጥ በርካታና ጥልቀት ያላቸው  የአዕምሮ አሠራር ሁነቶችን እየሰነገ ያስገባል። ለዋቢ ያህል ስለ “ኦቲዝም” እና ስላገር አመራር የተካሄዱትን ውይይቶች ማንሳት ይቻላል። አንዳንዶች “የትረካውን ፍሰት አደናቀፈብኝ” ሊሉ እንደሚቸሉ እረዳለሁ። ወይንም የሰበካ ያህል ሊቆጥሩት እነደሚችሉ እገምታለሁ።  በበኩሌ ግን በደራሲው የዕውቀት ደረጃ ያሉና የነበሩ ሰዎች ፀጋቸውን በልቦለድ ትረካ አጊጠው ሲያካፍሉን አይቸ አላውቅምና ሥራውን እጅግ በጣም ነው የወድኩት። አድናቂውም ሆኛለሁ።ይህን አስተያዬት ስሰነዝር የማተሚያ ቤት ልምዴንና ከደራሲያን ጋር ለመዋል ያጋጠምኝን  ሰፊ እድል ዋቢ ጠርቸ ነው።

   “የተቆለፈበት ቁልፍ” ባወቃቀርም በሴራም ደረጃ የተዋጣለት ሥራ ስለሆነ ነው ባንድ ዓመት እድሜ ለሶስተኛ እትም የበቃው።  በቀድሞዎቹ ዘመናት ለሁለተኛና ሦስተኛ እትም የበቁ ደራሲያን በጣት መቆጠራቸውን ግንዛቤ ስናስገባና ባሁኑ ዘመን ደግሞ እንደነ ይስማእከ (ዴርቶጋዳ) ያሉ ደራሲያን ላሥረኛ እትም መብቃታቸውን ስናይ የመግዛት አቅም ያለውና የተማረው ሕበረተሰባችን መስፋቱን እንረዳለን። ይህ ታዲያ ደራሲያንን ሊያበረታታ ይገባል። ደራሲ ተጨንቆና ተጠቦ የሚጽፈው ሥራው ይነበብለት ዘንድ ባለው ምኞት ተገፋፍቶ ነው። ሌሎች እንደ ዓላማ የሚጠቀሱ አነሳሾች በኔም በብዙዎችም ዘንድ ሚዛን አይደፉም።  በዚህ ረገድ ደራሲ ምሕረት ደበበ ባገኘው ተቀባይነት በጅጉ መደሰት አለበት። የሚቀጥለው ሥራው በዚህኛው ስኬት ተበረታትቶና ባገኘው ልምድ ይበልጡን በልጽጎ እነደሚቀርብ አልጠራጠርምና “በርታ!” እለዋለሁ።

 


November 14, 2014