Wednesday, July 30, 2008

"በርግጥ ኢትዮጵያ ላይ ሴራ አለ?"

ይህን ጥያቄ የማነሳው ያለ ምክንያት አይደለም። ጥቂት በማልለው የሕብረተሰባችን ክፍልና አልፎ አልፎም ቢሆን በተቃዋሚ ፓርቲዎች አካባቢ ሲንጸባረቅ የማየው የውጭ ፖሊሲ አዝማሚያ ስለሚያሳስበኝ ነው።

ክርክሬን አጭርና ደፋር በሆነ ዓረፍተ ነገር ልክፈትና “ታላላቅ መንግሥታት የኢትዮጵያን መጠናከርና አንድነት አይፈልጉም” የሚለው አመለካከት ከዘመናችን የፖለቲካ ጭብጥ ጋር የማይገናዘብ በማስረጃ ያልተደገፈ አጉል ስጋት ነው እላለሁ።

ከጭብጡ ጋር የማይገናዘብ ያልኩት ያለንበት ዘመን የኮሎኒያሊዝም መስፋፋትና “አፍሪካን የመቀራመት” ዘመቻ ያከተመበት መሆኑን ለማመልከት ነው። በዚያ ዘመን ኢትዮጵያን ለማዳከምና ግዛቷን ከዚህም ከዚያም ለመቦጨቅ የተጉ መንግሥታት በርካታ ነበሩ። ኢጣልያ፤ እንግሊዝ፤ ፈረንሳይ፤ ቱርክና ግብጽ ማለቂያ በሌለው ጦርነት ውስጥ ጠምደውን ለልማት የምናውለውን ውድ ጊዜና ሀብት ሰርቀውብናል። በሁለተኛ ደረጃ የሚታይ ይሁን እንጅ ግብጽና ሱዳን ዓባይ ወንዝን በተመለከተ ብዙ ይፈታተኑናል። ባካባቢው ከፍተኛ የክርስትና ሀይማኖት ተከታይ የሚገኝባት አገር በመሆኗም አንዳንድ የስልምና ሀይማኖት ተከታይ አገሮች ኢትዮጵያን በፍቅር አያይዋትም። የኋለኞቹ በየራሳቸው ችግር የተጠመዱና ከኃያላን ጋር የማይመደቡ በመሆናቸው ለጊዜው አላተኩርባቸውም።

ዘመኑ የተለዬ ነው፤
አሁን የምንገኘው ፈጽሞ ልዩ በሆነ የዓለም ፖለቲካ ድባብ ስር ስለሆነ የፈለግነውን ያህል ብንጠራጠር፤ ባለፈው በደላችን ላይ ብናላዝንና ብናቄም ላዲሱ ዓለም የኑሮ ፈተናችን የሚጠቅመን ነገር የለም። የዚህ ትውልድ አደራ በመቃ ብዕር የተጻፈና በብራና ላይ የተከተበ ሳይሆን በኮምፒውተር ግራፊክ የተቀረፀ የ21ኛው ክፍለዘመን አደራ ነው።

እራስ የሚያዞር ጥድፊያና በጀርባ የሚያርድ ተወዳዳሪ በበዛባት ዓለም የሀገራችንን ድርሻ ለመሻማትም ሆነ የክብር ቦታዋን ለማግኘት የምናደርገው ትጋት ፋታ መስጠት የለበትም። መመራመር ያለብን ያዲሱ ዓለም የፖለቲካና የኤኮኖሚ ድባብ ምን ይመስላል? በዚህ ድባብ ውስጥ ሁነኛ ተጫዋች ሆነን ለመገኘት በማሕበረሰብ ደርጃ ባቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ምን ዝግጅት ማድረግ አለብን? በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ከማን ጋር መሻረክ ይኖርብናል? የፓለቲካና የኤኮኖሚ ፖሊሲዎቻችን ወዳጅ፤ ካፒታልና የቴክኖሎጅ ፍሰት እንዲስቡ ምን ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለብን እያልን ነው። ለሁለተኛ ጊዜ “በረሳነው ዓለም እንድንረሳ” መፍቀድ የራስን ሕይወት በራስ የማጥፋት ያህል ሀጢአት ይመስለኛል።

በመነሻነት ይህን ያህል ካልኩ በኋላ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውጭ መንግሥታትን ድጋፍ ለማግኘት፤ በተለይም ደግሞ ወሳኝ ሚና የሚጫወተውን ያሜሪካን መንግሥት ድጋፍና አመኔታ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አመርቂ ነበር ወይ? የሚለውን ልመልከት። መልዕክቴን በቅጡ ለማስተላለፍ ይረዳኝ ዘንድ ጥረታቸው “በቂ አልነበረም” በሚል ድምዳሜ እጀምራለሁ።

የተቃዋሚ ወገኖችና ያሜሪካ አስተዳደር መቃቃር፤
ቁጥሩ ትንሽ የማይባል የዳያስፖራ ነዋሪ፤ እንዲሁም ብዙ የፓርቲ፤ የሀይማኖትና የማሕበራዊ ድርጅት መሪዎች “ታላላቅ መንግሥታት ኢትዮጵያን በማፈራረስ ወይንም በማዳከም ሴራ ውስጥ አሉበት” የሚል አስተሳሰብ ያንጸባርቃሉ። የዚህ ሀሳብ አራማጆች በዋቢነት የሚጠቅሱት ሶማሊያ በ1974 ኢትዮጵያን ስትወር አሜሪካ የተከፈለበትን መሣሪያ አላስረክብም ማለቷን፤ እንዲሁም ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚባል ገንጣይ ቡድን በ1991 አገሪቷን እንዲቆጣጠር መፍቅዳቸውን ነው። ወደኋላ ከተመለስን ሌሎችም ይኖራሉ።

ይሁን እንጅ አሜሪካ ለምን እነዚህን አቋሞች እንደወሰደች፤ ይህ ደግሞ ከራሷ ብሔራዊ ጥቅም አንጻር ለምን ትክክል ነው ብላ እንዳሰበችና ፖሊሲዋ ኢትዮጵያንም ሌሎች አገሮችንም በሚመለከት ወጥነት እንዳለው መረዳት አለብን።

የ1974ቱ አብዮት የኮሚኒዝም ጽንስና የብሔርተኝነት ዝንባሌ ይነበብበት ስለነበር አሜሪካኖቹን ቢያቁነጠንጣቸው አያስገርምም ነበር። ከዚህም ሌላ ሶቪየት ዩኒየን የሶማሊያ ቆይታዋን በማቋረጥ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ ለማዞር እንደተዘጋጀች አሜሪካ ታውቅ ነበርና መሣሪያ መላኩን አቆመች። በዚህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ የቀረው አማራጭ ጭልጥ ብሎ ከሶቪዬት ጉያ መግባት ሆነ።

ስለብሔርተኝነት ካነሳን አሜሪካም ሆነች ሌሎቹ ኃያላን መንግሥታት ብሔርተኝነት፤ በተለይ ደግሞ አክራሪ ዓይነቱ ብሔርተኝነት ለምን እንደሚገዳቸው መረዳት ያስፈልጋል። ብሔርተኝነት በባህርይው ገለልተኛና አትንኩኝ ባይ መሆኑ፤ አክራሪ ብሔርተኝነት በዓለም ታሪክ ውስጥ ብዙ ጥፋት ማስከተሉ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ አክራሪ ብሔርተኛ መንግሥት ባለበት አካባቢ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ እንቅፋት ስለሚሆንባቸው ፈጽሞ አይፈቅዱትም።

ወደሁለተኛው የቅሬታ መንስዔ ልሸጋገር። ብዙ ሰዎች እንደሚያስቡት አሜሪካ ሕወሀት ሙሉ ሥልጣን እንዲጨብጥ አትፈልግም ነበር። “ሕውሀት በአንድ አነስተኛ ብሔረተስብ የተገነባ ፓርቲ ስለሆነ ሰፊ የሕዝብ መሠረት አይኖረውም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕውሀትን የሚመለከተው እንደ ተገንጣይ/አስገንጣይ ሃይል ነውና አመኔታውን አይለግሰውም፤ ራሱ ሕውሀት ጥርሱን ነቅሎ ያደገው በአልባኒያ ኮሚኒስት ፓርቲ ሞግዚትነት ስለሆነ መልካም አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ ለማምጣቱ ምን ማረጋገጫ አለን?” የሚሉ ተጨባጭ ስጋቶችን ታስተናግድ ነበር።

የለንደኑ ድርድር፤
ከነዚህ ስጋቶች በመነሳት ነበር አሜሪካ ሕውሀትንና በመፈራረስ ላይ የነበረውን የሁለቱ ተስፋዬዎች መንግሥት (ጀኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳንና አቶ ተስፋዬ ዲንቃ) ጥምር የሺግግር አስተዳደር እንዲያቋቁሙ ጥረት ያደረገችው። ሕውሀትና የነተስፋዬ መንግሥት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ይዘውት የቀረቡት አቋም የተለያየ ቢሆንም ለማቀራረብ የማይቻል አልነበረም። በብዙ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ተደርሶ በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ የጦር ሚኒስቴርን ማን ይቆጣጠርና በሕይዎት ማጥፋት የሚጠየቁ የደርግ ባለሥልጣናት ሁኔታ በምን መልክ ይታይ የሚሉት ጥያቄዎች ድርድርሩን እንዳቆረፈዱት ይነገራል። ይህ በመካሄድ ላይ እያለ በመላ አገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ውስጥ ሊፈነዳ የተቃረበ የፀጥታ ሁኔታ ተፈጠረ። አሜሪካኖቹ ለዚህ አሳሳቢ ሁኔታ ቅድሚያ ሰጡና ፀጥታ ለማስከበር የተሻለ ድርጅት የነበረው ሕውሀት ከተማዋን/ሀገሪቷን እንዲቆጣጠር ተስማሙ። “ጦሩ የተፈታውና የሕዝብ ድጋፍ ከድቶት የነበረው የነተስፋዬ መንግሥት በለንደኑ ውይይት ላይ በብልህነት ተደራድሮ ቢሆን ኖሮ ያገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ልዩ መልክ ሳይኖረው ይቀር ነበር?” እያልኩ አንዳንዴ ራሴን አካለሁ።

ታዲያ አሜሪካኖች ለሕውሀት የሰጡት ድጋፍ ገደብ ነበረው። በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ለማምጣት ግዴታ አስገብተውና ይህን ቃል የማያከብር ቢሆን የኤኮኖሚና የዲፕሎማሲ ድጋፍ እንደሚነፍጉት አስጠንቅቀው ነው። የኸርማን ኮኸን “ኖ ዴሞክራሲ ኖ ኤይድ” ከዚህ መነጨ።
እዚህ ላይ “ሕውሀት ላሜሪካኖቹ የገባውን ቃል ሲያፈርስ፤ ጸረ ዴሞክራሲና ጠባብ ፖሊሲዎቹን ሲያራምድ ለምን ካሮታቸውን አልነጠቁትም?” የሚል ጥያቄ ቢነሳ አግባብነት አለው። ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት በዲፕሎማሲው መስክ የምናየውን ግድፈት በማጥራት በኩል ይረዳል ብዬ ስለማምን አንዳንድ ነገሮችን አነሳለሁ። ቢያስደስትም ቢያስከፋም።

አንደኛ። አሜሪካ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ካላት የተንሰራፋ ጥቅም፤ ኃላፊነት፤ አቅምና ትዕግሥት አንጻር ለአፍሪካ የምትሰጠው ጊዜ እጅግ አነስተኛ ነው። ስለ አፍሪካም ሆነ ስለያገሮቻችን አበጥ ያለ አመለካከት ያለን ሁሉ ያን አመለካከታችንን ጥቂት ማስተንፈስ አለብን። ኤኮኖሚያዊና ስትራቴጅያዊ ጥቅማቸው አናሳ በሆነባቸው አገሮች የዴስክ ኃላፊ አድርገው የሚመድቧቸው ግልገል ዲፕሎማቶች መሆናቸውን ስናይ በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ያለን ቦታ የቱን ያህል የኮሰሰ እንደሆነ እንገነዘባለን።

ሁለተኛ። አሜሪካም ሆነች አውሮፓውያን ትኩረታቸውን የሚስብ አማራጭ ኃይል እስካላገኙ ድረስ ካለው መንግሥት ጋር መዳረቅን ይመርጣሉ። ለምን ብለው ጣጣ ውስጥ ይግቡ? “ተቃዋሚው የተበታተነና አብሮ ለመሥራት የማያመች ነው” እያሉ በመደጋገም ሲናገሩ የምንሰማው ለዚህ ነው። ኃያላን መንግሥታት በየትም አገር ቢሆን ጠንካራ አማራጭ ፓርቲ እንዲኖር መፈለጋቸው እርግጥ ነው። “ትራምፕ ካርድ” ይሉታል እነሱ። ዛሬ አንዱን ነገ ሌላውን ጠጋ በማድረግ ባገሪቱ ላይ ያላቸውን ፖሊሲና ፕሮግራም ያለ ብዙ ውዝግብ ለማራመድ የሚያመቻቸው አማራጭ ሲኖራቸው ነውና። አለያ የ “ስታተስ ኰ ፖለቲካ” መከተላቸውን ይቀጥላሉ።

ሦስተኛ። የዲፕሎማቲክ ፖሊሲ የሚቀረጸው በርካታ ነባራዊ ሁኔታዎች ተገናዝበው ነው። ሀቅ፤ የሞራል እሴቶችና የሕገመንግሥት አንቀጾች ብዙ ሚዛን ላይደፉ ይችላሉ። አሜሪካ በሕገመንግሥቷ ዴሞክራሲን ለማስፋፋትና ለመብት የሚታገሉ ሕዝቦችን ለመርዳት የገባችውን ክቡር ቃል ኪዳን ችላ እያለች አንዳንዴ ከአምባገነኖች ጋር ስትወግን የምናየው አምባገነኖች ስለሚጥሟት ሳይሆን ሁነኛ አማራጭ ስለምታጣ ነው።

ወደለንደኑ ጉባኤ ልመለስና ሌላ አሜሪካኖቹን ያነሆለለ አንድ ግንዛቤ ነበር። “የሕውሀት ኃይል የተገነባው ጠባብ የብሔረሰብ መሠረት ላይ ስለሆነ የሌሎች ብሔረሰቦችን ድጋፍና አመኔታ ለማግኘትም ሆነ ሁነኛ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ ለመቆየት በዴሞክራሲ ፋና-ወጊነት የታሪክ ቦታ መቅረጽ ይፈልጋል። ከረጅም ጊዜ ጥቅሙ አንጻር ሲታይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባለውለታ ማድረግ “ደ!” የሚያሰኝ ጥያቄ ነው” የሚል ሎጅክ-ቀመስ ነገር ግን ገራገርነት የሚነበብበት አቋም ወሰዱ። ኸርማን ኮኸን ስቴት ዲፓርትመንትን ከለቀቁ በኋላ በጻፉት መጽሀፍ ይህ ግንዛቤ ግድፈት እንደነበረውና ሕውሀት ቃሉን ያልጠበቀ አምባገነን መንግሥት መሆኑን በምሬት ገልጸዋል።

በላይኛው የጽሁፌ ክፍል አሜሪካኖቹ ለወሰዱት አቋም ምንና ምን ታሳቢ አድርገው እንደነበር የማውቀውንና የሚመሰለኝን ያህል ላስጨብጥ ሞክሬያለሁ። ዛሬ ላይ ሆኘ ሳየው በአጭሩ ጊዜ አሜሪካ ያገሯን ጥቅም ችላ ብላ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ስርጸት መቆም ይገባታል እያልን ባደባባይ መዝለፋችን ትክክል አልነበረም፤ ያተረፍነው ነገር የለምና። በሌላ በኩል ደግሞ አሜሪካኖቹ የሕውሀት ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነው ተቃዋሚው ወገን አክራሪ ብሔርተኛ ነው፤ የደርግ ርዝራዥ ነው፤ የአማራ ስብስብ ነው በሚል አሳፋሪ የቀለም ቅብ ውስጥ መሳተፋቸው የጥፋትም ጥፋት ነበር።


ላጠቃል፤
ታላላቅ መንግሥታት በኢትዮጵያ መዳከምም ሆነ መበታተን የሚጠቀሙት አንዳችም ነገር ስለሌለ ይህን ዘመን ያፈጀ አስተሳሰብ መላቀቅ አለብን። በኤኮኖሚና በሚሊተሪ የዳበረች፤ ላካባቢው መረጋጋት አስተማማኝ ኃይልና አጋር የምትሆን ኢትዮጵያን ይመርጣሉ ብሎ ማሰብ ይበልጡን ሚዛን ይደፋል። ከዚህም ሌላ 80 ሚሊዮን ሕዝብ ሠላምና መረጋጋትን አግኝቶ የነፍስ ወከፍ ገቢውን ቢያሳድግ ታላቅ ገበያና ታላቅ ወገን ተፈጠረ ማለት ነውና አሜሪካም ሆነች ሌሎቹ አይከፉም። በአንጻሩ ደግሞ ከኢትዮጵያ መራብ ያሚተርፋቸው ነጻ የስንዴ ርዳታ ማመላለስ ብቻ ነው። ከኢትዮጵያ የእርስ-በርስ ግጭት የሚያገኙት በሚዘገንን የነፍስ አድን ዘመቻ ውስጥ መዘፈቅ ብቻ ነው።

ራዕያችን በምንመኘው ደረጃ ድጋፍ ሳያስገኝ ቀርቶ ከሆነ ጥፋቱ የኛ እንጅ የነርሱ አይመስለኝም። ራዕይ ስሜትን በሚነካ መልክ ተቀርጾ፤ በማለፊያ የዲፕሎማሲ ጥበብ ተጠቅልሎ ከተወዳዳሪ ራዕዮች በልጦ መገኘት አለበት። የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ጥረታችን “የኛን ሀሳብ ተቀበሉን፤ የኛን ጭኸት ስሙን” ከሚለው ረድፍ ወጥቶ ለምንና በምን ምክንያት እኛ የተሻልን አማራጭ እንደሆንን፤ እንዴትስ የፖለቲካ፤ የኤኮኖሚ፤ የዕምነት፤ የስትራቴጅና የደህንነት መሥመራችን ከነርሱ መስመር ጋር እንደሚጣጣም በማሳመን ላይ ያተኮረ ሊሆን ይገባል።

በሌላ በኩል ደግሞ ራዕይና ፖሊሲ ጥቅል ስለሆኑ “ግሩም!” ከመባል ያለፈ አድናቆትን አያስገኙም። ቁምነገሩ ያለው ከዝርዝሩና ፈረንጆቹ “ብርንዶውን አሳየኝ” ከሚሉት ላይ ነውና ያፈጻጸም ፕላንና ይህን በተግባር ለመተርጎም የሚችል ሰፊ የድጋፍ መሠረት ያለው ድርጅት እንዳለን ማሳመን ግዴታችን ይሆናል።

ድጋፍ ማግኘትና አጋር ማብዛት ብዙ ሥራ፤ ብዙ ስልት፤ ብዙ አንደበተ-ርቱዕ ዲፕሎማቶች፤ ብዙ ትዕግሥትና ብዙ ሺር-ጉድ ይጠይቃል። ኃያላን መንግሥታት ሳይቀሩ አንዱ በሌላው ላይ ካልተደገፈ ብቻቸውን መቆም አይችሉምና የወዳጅ ክበባችንን በውል እናስፋ። ይህ “በራስ መተማመን” የምንለውን ክቡር መርህ የሚያኮስስ ሳይሆን ውጤታማነቱን የሚያፋጥን መሆኑንም አንሳት።

ወዘተርፈ…(የኦባማ ጉዳይ)
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን ያገባደዱት ያሜሪካ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴቪድ ክሬመር ኢትዮጵያን በተመለከተ ያሜሪካ የውጭ ፖሊሲ መሠረታዊ ለውጥ እንደማይኖረው አስገንዝበዋል። ከኦባማ መመረጥ ጋር ብዙ ተስፋ ለምናደርግ ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይመስለኛል።

ዴቪድ ክሬመር ድረስ ሳልሄድ በጥልቅ ትንታኔውና በወዛም አቀራረቡ የሚታወቀው የኛው “ኢትዮ ፐንዲት” www.http://ethiopundit.blogspot.com/ ጁን 29 ባስነበበው ጽሑፍ ኢትዮጵያን በተመለከተ ያሜሪካ ፖሊሲ ይለወጣል ብሎ ማሰብ አደጋ እንዳለው አስጠንቅቋል። “ዴሞክራቶቹ ቢል ክሊንተን፤ ማደሊን ኦልብራይት እና ሱዛን ራይስ ከመለስ ዜናዊ ጋር የነበራቸው መሞዳሞድ በሪፐብሊካኑም አስተዳደር ቀጥሎ ቡሺ፤ ኮንደሊዛ ራይስ፤ ቪኪ ሄንደርሰንና ጀንዳይ ፍሬዘርም የመለስ አሳዳሪ ሆነው ሰንብተዋል” ይላል። በመቀጠልም “ጆን ማኬን ከዚህ የተለየ ፖሊሲ ይከተላል ብሎ ማሰብና የመለስ ደጋፊና አሁን የባራክ ኦባማ የውጭ ግንኙነት አማካሪ ሆና የምታገለግለው ሱዛን ራይስ ኦባማ በዜናዊ ላይ ፊቱን እንዲያዞር ትማጸናለች ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው” በማለት ይደመድማል።

አዘለም አንጠለጠለም መልዕክቱ ፓርቲዎች ቢለዋወጡ እንኳ ያሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ይህን ያህል መሥመሩን አይስትም ለማለት ነው። ገና ብዙ ሥራ ይጠብቀናል ለማለትም ነው።

kuchiye@gmail.com

Friday, July 11, 2008

“ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ? - እንካ ስላንቲያዎቹ!”


ሰሞኑን በድሕረ ገጾች ላይ የማነባቸው አስተያየቶችና ትችቶች ሁለት ቤሳ የምታወጣ ሀሳቤን እንዳካፍል ገፋፉኝ። ግርማ ካሣ “ኢሕአዴግን ማስወገድ ወይስ መለወጥ?” በሚል፤ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ ደግሞ “ሕብረትን በማስቀደም…” ሮቤል አባብያ “አንድነት ፓርቲ ለሚከተለው የሠላም ጎዳና ይሁን ብለናል” በሚሉ ርዕሶች ያስነበቡን ሰነዶች “ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ ትግል” በሚለው ትኩስ መነጋገሪያ ንጥብ ዙሪያ የሚያንዣብቡ ናቸው። እነዚህንና ሌሎችንም ጽሁፎች በ http://abugidainfo.com/ እና በሌሎች ድሕረገጾች ማንበብ ይቻላል።

ነገሬን አጭር እና ግልጽ-ያለ ለማድረግ እሞክራለሁ። “ከንግዲህ ሠላማዊ ትግል አያዋጣም” ብለው የተነሱትና ግንቦት 7 የሚባለውን ድርጅት የፈጠሩት ወገኖች እስከትናንት ድረስ በሠላማዊ ትግል ይምሉ እንደነበር አያከራክርም። ሞኝ፤ ወረቅት፤ ቴፕና ቪዲዮ ያስያዟቸውን አይለቁምና ማስረጃዎች ሞልተዋል። የሰሞኑ እንካ-ስላንቲያ የጫራቸው ርዕሶች የቱን ያህል ነርቭ-ነክ ቢሆኑም መንገዳችንን አጥርተን ለመጓዝ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ስላላቸው እንዲድበሰበሱ መማጸን ትክክል አይመስለኝም።

የግንቦት 7 ንቅናቄ መቋቋም ለምን አወዛጋቢ ሆነ?
እራሴን ፕሮግሬሲቭ ከሚባለው አምባ ልደብልና “ማንም ሰው የፈለገውን የኑሮ ወይንም የትግል ጎዳና ለመምረጥ ያለውን መብት አከብራለሁ” ልበል። የናንተን አላውቅም እንጅ አንዳንዴ ይህ አባባል ስድ ፍካሬ ሆኖ አገኘዋለሁ። ግለሰቦች እራሳቸውን ብቻ የሚመለከት የሕይወት ምርጫ ቢያደርጉ የሚጠቅሙትም የሚጎዱትም ያው ራሳቸውን ብቻ ስለሆነ ለዚህ ዓይነቱ ምርጫ ቁብ ሊኖረን አይገባም። ከግለሰብ አልፎ ማሕበረሰብንና ሀገራዊ እንቅስቃሴን በሚነካ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ውሳኔ ግን ጉዳያችን ይሆናል።

ከዚህ አንጻር የሕዝብን አመኔታና አደራ የተቀበሉ መሪዎች የሚያደርጉት ውሳኔ የተከታዮቻቸውን ፍላጎትና ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት አያከራክረንም። ግልጽነትና ተጠያቂነት መመሪያዎቻችን ይሆናሉ ብለው ምህላ ፈጽመውልናልና። “ሠላማዊ ወይንም ትጥቅ” በሚል ዓቢይ ጥያቄ ላይ አንድ ወይንም ሁለት ሰዎች ሆነው ውሳኔ ካደረጉ በኋላ የይስሙላ ወረቀት በትነው “ኑ ተከተሉን!” ቢሉ ለሕብረተሰቡ ያላቸውን ንቀት ከማንጸባረቅ በስተቀር ሌላ የሚያመላክተው ነገር የለም። የሀይሉ ሻውል ችግር ይህ ነበር፤ ከልክ በላይ ወጠርከው አትበሉኝና መለስ ዜናዊና ሥዩም መሥፍን ከሱዳን ጋር ያደረጉት ስምምነትም ከዚህ አሠራር ብዙ የተለዬ አይደለም።

እንዲመራኝ የምመኘው ሰው፤ ይልቁንም ደግሞ ድጋፌን የሚሻ ፖለቲከኛ በራዕይ ጥራት፤ በሀቀኝነት፤ በመልካም ስነምግባርና በታማኝነት ባህርዮች የታነጸ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ከዕብሪትና ከመሠሪ ጠባዮች የጸዳ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ባስቀመጥሁት ቦታ እንዳገኘው እፈልጋለሁ። ዛሬ እዚህ ነገ እዚያ የሚሉ ሰዎች የምይዘውንና የምጨብጠውን ያሳጡኛልና ቀልቤ አይቀበላቸውም።

አንደኛው የግንቦት 7 መሪ “ሠላማዊ ትግል ከንቱ ነው” ከሚለው ድምዳሜ ላይ የደረሱት እስር ቤት እያሉ እንደነበር ሰምተናል። ይህ ከሆነ ደግሞ በሰላማዊ ትግል ከሚያምነው የቅንጅት አመራር ጋር በአሜሪካን አገር መድረክ መቋደስ አልነበረባቸውም። የጉዞ ፕሮግራሙ መገባደጃ ድረስ ይህን ያህል ግዙፍ ምስጢር ከትግል ጓዶች ደብቆ ማቆየት መልካም የማኔጅመንትና የወዳጅነት ባህርይ አይነበብበትም።

የመሪዎች ባሕርይ ሊቆረቁረን ይገባል ወይ?
ፈረንጆቹ በጣም ሊቆረቁረን ይገባል ይላሉ። መሪ ልሁን ብሎ የሚነሳን ሰው ከነአስተዳደጉ፤ ከነመሠረታዊ ዕምነቶቹ፤ ከነታሪከ ምግባሩ አበጥሮ ማወቅ ወደፊት ሊከሰት ከሚችል አደጋና ፀፀት ይሰውራል - ሙሉበሙሉ ባይሆንም በጅጉ ይሰውራል። ለነገሩ ይህ ብልህነት የፈረንጆች ብቻ አይደለም። ያገሬ ሰው በሲራራ ነጋዴነት አብሮት የሚዘምትን ሰው እንኳ በቅጡ ካላጠናው ከቤቱ አይወጣም። ይችን ያህል ብልህነት እንዴት አጣን?

ለመሪነት የምናጫቸውን ሰዎች በቅጡ መመርመር ነውር የለውምና ይህን ለማድረግ ወኔው ሊኖረን ይገባል። ይህን ሳናደርግ እየቀረን ስንት ጊዜ እንደተበለጥን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ሞኝን እባብ የነከሰው ሁለቴ ነው ይባላል። አንዴ እባብ ምን እንደሆነ ሳያውቅ አንዴ ደግሞ ከልምዱ ባለመማሩ።

ሁለቱ ተጻራሪ ሀሳቦች ጎን ለጎን የመሄድ ዕድላቸውስ?
ብዙ አይመስለኝም። ግንቦት 7 ንቅናቄውን ከማወጁ በፊትና በኋላ በአባልነት ለመመልመል ሲባጅ የከረመው በሰላማዊ ትግል ዙሪያ የተሰባሰቡትን የቀድሞውን ቅንጅት ያሁኑን የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች ነው። እዚህም ላይ ትንሺ መሰሪነት ይታየኛል። ባንድ በኩል ለአንድነት መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ እያለ የትብብር ዘንባባ ይዘረጋል። በሌላ በኩል ደግሞ “ሠላማዊ ትግል በተባለው ርዕዮት ቀመስ ትብትብ የታነቀ ትግል” (አንዳርጋቸው ጽጌ) ማካሄድ ፋይዳ ቢስ ነው እያለ የሚሊዮኖችን ዕምነት ያንኳስሳል።

የ1997ቱ የዴሞክራሲ መስኮት ገርበብ ብሎ ከመከፈቱ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበረው የፖለቲካ መልክዓ ምድር ውስጥ ሕዝብን ማደራጀትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማብቃት ይቻላል ብለው የታገሉ ሰዎች ዛሬ ምን ሀሳባቸውን ሊያስለውጣቸው እንደሚችል አይገባኝም። የኢሕአዴግ ባሕርይ ትናንትም ዛሬም አንድ ነው። በጎሳ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ የሚያራምድ፤ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ በሽታ የተጠናወተው፤ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን የሚረግጥ መንግሥት ነው።

ይህን ሁሉ እያወቅን ነው ሥርዓቱን በሠላማዊ ትግል መለወጥ እንችላለን ብለን የተነሳነው። የ97ቱ የዴሞክራሲ ቀዳዳ የተከፈተው ሕዝብ፤ ፓርቲዎች፤ ነጻው ፕሬስና ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በኢሕአዴግ ላይ ባሳደሩት ተጽዕኖ ነበር። ኢሕአዴግ የተከፈተውን ቀዳዳ ዘግቶ ለማቆየት የሚያስችል አቅምና ምቹ የፖለቲካ ምልክአ ምድር እንደሌለው ማመን አለብን። ሕብረተሰቡ መሀል የሰፈነ የሚመስለው ዝምታ አንድ የፖለቲካ ወይንም የኤኮኖሚ ቀውስ ሲፈጠር የሚለወጥ ነው። እየተደራጀና እያደራጀ በሕዝብ መሀል የሚቆይ ፓርቲ መኖሩ ለቀውጢዋ ቀን ያስፈልጋል።

የትጥቅ ትግል ከማይመረጥበት ምክንያቶች
የትጥቅ ትግል ኮሎኒያሊስቶችንና አምባገነኖችን ለማስወገድ በአማራጭነት ያገለገለው ዓለም በሁለት የፖለቲካ ማዕዘኖች በተከፈልችበት ዘመን ነበር። ለዚያውም ቢሆን አንድን አምባገነን በሌላ አምባገነን ከመተካት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም። ፋይዳ አስገኝቶ ከሆነም ከስንት አንድ ነውና ጂኦ-ፖለቲካው በተለወጠበት ባሁኑ ዘመን እንዳማራጭ መታየቱ ብልህነት ይጎድለዋል።

ሌላም አለ። ጎረቤት አገሮች መጠለያ መስጠት በማይፈልጉበት ዘመን፤ ከራስ ፀጉር የበዛ ሰላይ በከተማና በገጠር ነዋሪው መሀል ተሰግስጎ ባለበት ጊዜ፤ እልቆ መሳፍርት ያለው፤ በዘመናዊ መሣሪያና በሳተላይት መገናኛ የታጠቀ ሠራዊት በሚርመሰበስበት ሁኔታ፤ ምዕራባውያንና የቻይና መንግሥት እሹሩሩ የሚሉት ታዛዥ መንግሥት በነገሠበት ሁኔታ ለትጥቅ ትግል ምቹ አየር ያለ አይመስለኝም። እነዚህ የማያመቹ ሁኔታዎች የሚለወጡት መንግሥትን መውጫ ቀዳዳ የሚያሳጡ ኤኮኖሚያዊ፤ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲገኑ ነው። ያኔ የፖለቲካው ሜዳ የለወጣል።

ሳላነሳ ማለፍ የማልፈልገው ሌላ ነገርም አለ። በትክክል ገብቶኝ ከሆነ ግንቦት 7 የትጥቅንም የሠላማዊ መንገድንም የሚከተሉ ፓርቲዎችን አስተባብሬ ኢሕአዴግን አስወግዳለሁ የሚል ዓላማ ያለው ይመስለኛል። የትጥቅ ትግል ያካሂዳሉ ከሚባሉት መሀል ደግሞ ኦነግና ኦብነግ ሳይኖሩበት አይቀርም። ታዲያ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በኢትዮጵያ አንድነት የማያምኑ መሆናቸው ሲታወቅ ከነርሱ ጋር ማሕበር መጠጣቱ ለምን ግብ ነው? ኤኤፍዲ በተመሳሳይ ዓላማ ሲቋቋም ሁለቱን ድርጅቶች ወደ መሃል ማምጣት ይቻላል በሚል ታሳቢ እንደነበር ትዝ ይለኛል። የሁለት ዓመት ዕድል ተሰጥቷቸው ካቋማቸው ትንሽ እንኳ ፍንክች የማለት አዝማሚያ አለማሳየታቸው እንድንጠረጥራቸው አያደርገንም?

ይህንኑ ክርክር ልቀጥልበትና፤ የኢሕአዴግ መንግሥት በግንቦት 7ም በኦነግም በኦብነግም የትጥቅ ትግል (በአመጽ) ይወገድ እንበል። አመጹ በሚያስከትለው ትርምስ ውስጥ ኦነግና ኦብነግ ለዓመታት ሲያልሙ የነበረውን የመገንጠል ሀሳብ ቢያውጁ ማን ያቆማቸዋል? ይህ ዓይነቱ ትግል በሚፈጥረው ቀውጢ ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስከብር የተማከለ ሠራዊ እንደማይኖር ከወዲሁ መገመት አያዳግትም።

ከሁለት ገጽ በላይ ላለመጻፍ ለራሴ የገባሁትን ቃል ስላፈረስኩ ይቅርታ በመጠየቅ እዚሁ ላይ አቆማለሁ። አይደግመኝም።

Kuchiye@gmail.com