Sunday, May 09, 2010

“ነፃነትና ዳኝነት በኢትዮጵያ” - በስዬ አብርሃ


እንደ ግምገማ - ኩችዩ
“መጽሐፍ!” ሲሉት ሰፍ የሚል ከራማ ቢጤ አለብኝ መሰል ስዬ አብርሃ ደረሱ የተባለው መድብል እጄ እስኪገባ ቸኩዬ ነበር። ባገራችን የቅርብ ዘመን ታሪክ ላይ አሻራቸውን ካተሙት ጥቂት ስዎች መሀል ናቸውና እኒህ ሰው የሚሉትን ለማወቅ ብተጋ አይፈረድኝም። ጀመርሁ የሚሉት የሁለተኛው ምዕራፍ ጉዟቸው የምንፈልገው ዓይነት መሆኑን የሚያመላክቱ ፍንጮች ያዘለ ሊሆን ስለሚችልም መጽሐፉን ለማንበብ በቂ ምክንያት አለ። ላወቀበት በመስመሮቹ መሀል የተሰነጉትን ሁሉ መመርመር ነው።

የትኛውም የሥነ-ጽሑፍ ሥራ ከወቅት ጋር ባለው ተዛምዶ መነበብ አለበትና ደራሲው ለምንና አሁን መናገር ፈለጉ? የሚለውን ለመመለስ ሞክሬያአለሁ። አንድም የጎደፈ ስምን ለማጽዳት፤ አንድም የገዘፈ ችግር አገራዊ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድርግ፤ አንድም ላዲስ የፖለቲካ ግብ መደላድል ለመፍጠር፤ አንድም ደግሞ ለበቀል ሊሆን ይችላል አልኩ። የጠቀስኳቸው አነሳሾች ነውር ወይንም መሰሪነት አላቸው ለማለት አይደለም። ያ እያንዳንዱ አንባቢ በየበኩሉ የሚደርስበት ድምዳሜ ነው።

ሌላው ታሳቢ ደግሞ ከደራሲው ጀርባ-አጥንት ጋር ተያይዞ ብቅ የሚለው የጥርጣሬ መንፈስ ይመስለኛል። በዚህ ረገድ ብዙዎቻችን እንደ ጎጃሙ ገበሬ እንደ ተክለዬስ የፖለቲካ ሰዎችን የምናየው በጎሪጥ ነው። እንኳንስ እኛ የሶስተኛ ዓለም ሰዎች ያንደኛ ዓለሙ ያሜሪካ ሕዝብ 70% ያህሉ በፖለቲከኞች ላይ ዕምነት አጥቶ የለም እንዴ? የነስዬ ጉዳይ ከተነሳ ደግሞ ነገሩ በመጠኑ ወሰብሰብ ይላል። ከብሔር ፖለቲካ ካምፕ ወደ ሕብረብሔር ፖለቲካ ካምፕ የዘለለን ሰው ባንዴ ሊያቅፉት ያሰቸግራልና ለተወሰነ ጊዜ በጥርጣሬ ዳመና ተከበው መሥራታቸው የማይቀር ነው። የጨዋታው ሕግ ስለሆነ ይህን አይስቱትም በዬ እገምታለሁ።

ይሁን እንጅ፤ የኔዋ የጥርጣሬ ዳመና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እየመዘነች፤ ደረጃ በደረጃ እየጠራች ለመሄድ የተዘጋጀች ናት። እንደምንም ብዬ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረስኳት ይምስለኛል። ሚዛናዊነቷ ደግሞ ለየትኛውም ወገኔ ነው። ተስፋ በትናንት ላይ ሳይሆን በዛሬውና በወደፊቱ ውሎ ላይ የሚገንባ እሴት ነውና ዝንተ-ዓለም የጥርጣሬ ተገዥ ልንሆን አይገባም ከሚሉት ወገን ነኝ። ቁም ነገሩም፤ ብልህነቱም ያለው አዕምሮን አትግቶ ልብን ከፍቶ ማዳምጡ ላይ እንጂ ማለቂያ ለሌው የ “ጠርጥር!” ባህል ተገዥ እመሆን ላይ አይደለም። ይህን ማድረግ ያልቻለ ህሊና ራሱን ቢታዘብ ይሻለዋል።

እንግዲህ ሁሌም እንደማደርገው መጽሐፉ ወስጥ ቀልቤን ከሳቡት መሀከል አንድ-ሦስቱ ላይ ላብራባችው። የቀሩትን ለማወቅ ገዘቶ ማንበብ ነው ወዳጄ! - ገቢው ለአንድነት አይደል?

“በደል ደርሶብኛል! ንጽህናዬ ሊታወቅልኝ ይገባል! ማስረጃዬም ይኸው!” ብሎ ወደ ህሊና አደባባይ የሚመጣ ሰው በመሠረቱ ሊከበር ይገባል - በታሪካችን ውሰጥ ይህን ያደረጉ ብዙ አይደሉምና። ካላችሁስ ጥርጣሬን ማጠንከር ተከሶና ታምቶ ፀጥ በሚለው ላይ ነው።

ደራሲው ስዬ ነገሮችን እንደማያደባልቁ በመጽሐፉ ምርቃት ላይ አሳውቀዋል። ህዝብ ከርሳችው የሚጠብቀው “የሕወሀትን ታሪክ፤ ወሰጠ-ነገሩን፤ ውጣ-ውረዱን፤ ሹም-ሺሩን… ወዘተ እንድተርክለት መሆኑን አውቃለሁ” ብለዋል። ዕድሜውን ከሰጣቸው ለታሪክና ለተመክሮ ቅርስ የሚሆኑ ፅሁፎች እንደሚያቀርቡም ቃል ገብተዋል። ሰለሆነም ለጊዜው ልንተቻቸው የምንችለው ለህትመት ባበቁት “ነፃነትና ዳኝነት በኢትዮጵያ” በሚለው አቅርቦት ላይ ብቻ ነው።

እንደኛ ባለ አገር ዳኝንት በገዥው ፓርቲና በመንግሥት ተጽእኖ ውስጥ ለመሆኑ ክርክር የሚያስፈልገው አይመስለኝም - የሁዋላ-ቀርነታችንም ሆነ የንዝንዛችን መነሻ ይኽው ነው። ያቶ ስዬ መጽሃፍ የችሎቱንና የእሥር ቤቱን ድራማ የሲኒማ ያህል ነው ቀርጾ የሚያሳየን። የደራሲው ተማጽኖ “በኔ ላይ የደረሰው የፍትህ መዛባት በመላ አገሪቱ ወስጥ ባሉ ወገኖቼ ላይ እየደረሰ ያለ ለመሆኑ ቋሚ ምስክር ነኝ!” የሚል ይመስላል። ከሌሎች ጋር ተዳምሮ፤ ይሄ ግንዛቤ በሰውዬው የፖለቲካ አስተሳሰብ ለውጥ ላይ ተጽዕኖ አላደረገም ማለት የሚቻል አይመስለኝም።

ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ተከሳሹን በእስር ለማቆየት ባንድ ጀምበር የወጣው ህግ፤ የብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት ፍትሀዊነት፤ ወጣቱ ዳኛ ባስተዳደሩ ለህግ አልገዛም ማለት የደረሰበት ብርቱ ፀፀት፤ የእስር ቤቶቹ መጨናነቅና የምሳሰሉት ገለፃዎች የሚያስደምሙም ቅስም የሚሰበሩም ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። መልዕክታቸውን ማሰተላለፍ ይችሉ ዘንድ ደራሲው ቋንቋውን ደህና አርገው ያስገበሩትም ይመስላል።

በሁለተኛ ደረጃ ያጤንሁትና ደራሲው በጽኑ እንዲታወቅላቸው የፈለጉት ጭብጥ ደግሞ በርሳቸው ቡድንና በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ቡድን መሀከል የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን አስመልክቶ የተፈጠረው ያቋም ልዩነት ሰለባ እንዳደረጋቸው ነው። “በህወሐት ውስጥ ለተከሰተው መሰነጣጠቅ ዋናው መንስኤ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ዙሪያ የተከሰተው ጦርነት ነበር” በማለት ፈርጠም አርገው ይከራከራሉ።

የነስዬ ወገን “የወራሪውን ጦር አከርካሪ መስበር የተያዘውን መሬት እርግጠኛ በሆነ መልኩ እንዲመለስ ያደርጋል፤ በኤርትራ የሚኖረው መንግሥት ለዘለቄታው በኢትዮጵያም ሆነ ባካባቢያችን የስጋት ጠንቅ ያልሆነና ልኩን ያወቀ እንዲሆን ያደረጋል…በሁለቱ አገሮች መሀከል በእንጥልጥል ያሉ ችግሮች ተፈትተው የሁለቱም ግንኙነት በጠንካራ መደላድል ላይ የሚገነባበት ሁኔታ ይፈጠራል” የሚል አቋም እንደነበረው ደራሲው ያስረዳሉ። ባንጻሩ ደግሞ ያቶ መለስ ቡድን፤ በተለይም አቶ መለስ ይህን የመከላከያ ጦርነት ዓላማ እነዳልደገፉና፤ ዓላማው በኢሕአዴግ ምክር ቤት ከጸደቀ በሗላም ለተፈጻሚነቱ መሰናክል እንደሆኑ ነው ጠንክረው የሚያትቱት። የገጽ ማዕቀቤ ብዙ እንዳትት አይፈቅድልኝምና ዝርዝሩን ከመጽሐፉ ብታገኙ ይሻላል እላለሁ።

መጽሐፉ እጅግ በርካታ በሆኑ ያገራችን ጉዳዮች ላይ ጮራ ይፈነጥቃል። በፖለቲካው፤ በማህበራዊው፤ በመንግሥት ቁንጮና በዙሪያው ስለተቀመጡት ሰዎች ምንነትና ማንነት፤ በረጅም ዘመን መከራ የተፈተነ ወዳጅነት ለህልውናና ለጥቅም እንዴት ተኖ እንደሚጠፋ፤ እነዚህን ሁሉ በመጽሀፉ ውሰጥ ከዳር እሰከዳር ተርከፍክፈው ታገኟቸዋላቸሁ። ከላይ እንደጠቆምሁት ደግሞ በመስመሮቹ መሀል የተሰነጉትን ፍንጮች በቅጡ መመርመር የሚችል ብዙ ያገኝበታል።

በመጨረሻም፤ ከሥነ ጽሑፍ አንፃር ልተች ብል አጉል እንዳልዳክር እሰጋለሁና ለነ አበራ ለማ ብተውላቸው ይሻል መሰለኝ። የደራሲ ማሞ ለማን “የወገን ጦር ትዝታዬ” እንዴት እነዳሳመረው ትዝ ይላችሁ የለም? www.abugidainfo.com/amharic/?p=3094. (በነገራችን ላይ - ዓይኔ ነው ወይስ ኢትዮ ሚዲያ መዝገብ-ቤት የለውም?)

“Freedom & Justice in Ethiopia” - By Siye Abraha
Book Review by Kuchiye
kuchiye@gmail.com
May 8, 2010