Friday, July 11, 2008

“ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ? - እንካ ስላንቲያዎቹ!”


ሰሞኑን በድሕረ ገጾች ላይ የማነባቸው አስተያየቶችና ትችቶች ሁለት ቤሳ የምታወጣ ሀሳቤን እንዳካፍል ገፋፉኝ። ግርማ ካሣ “ኢሕአዴግን ማስወገድ ወይስ መለወጥ?” በሚል፤ ፕሮፌሰር ማሞ ሙጨ ደግሞ “ሕብረትን በማስቀደም…” ሮቤል አባብያ “አንድነት ፓርቲ ለሚከተለው የሠላም ጎዳና ይሁን ብለናል” በሚሉ ርዕሶች ያስነበቡን ሰነዶች “ሠላማዊ ወይስ ትጥቅ ትግል” በሚለው ትኩስ መነጋገሪያ ንጥብ ዙሪያ የሚያንዣብቡ ናቸው። እነዚህንና ሌሎችንም ጽሁፎች በ http://abugidainfo.com/ እና በሌሎች ድሕረገጾች ማንበብ ይቻላል።

ነገሬን አጭር እና ግልጽ-ያለ ለማድረግ እሞክራለሁ። “ከንግዲህ ሠላማዊ ትግል አያዋጣም” ብለው የተነሱትና ግንቦት 7 የሚባለውን ድርጅት የፈጠሩት ወገኖች እስከትናንት ድረስ በሠላማዊ ትግል ይምሉ እንደነበር አያከራክርም። ሞኝ፤ ወረቅት፤ ቴፕና ቪዲዮ ያስያዟቸውን አይለቁምና ማስረጃዎች ሞልተዋል። የሰሞኑ እንካ-ስላንቲያ የጫራቸው ርዕሶች የቱን ያህል ነርቭ-ነክ ቢሆኑም መንገዳችንን አጥርተን ለመጓዝ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ ስላላቸው እንዲድበሰበሱ መማጸን ትክክል አይመስለኝም።

የግንቦት 7 ንቅናቄ መቋቋም ለምን አወዛጋቢ ሆነ?
እራሴን ፕሮግሬሲቭ ከሚባለው አምባ ልደብልና “ማንም ሰው የፈለገውን የኑሮ ወይንም የትግል ጎዳና ለመምረጥ ያለውን መብት አከብራለሁ” ልበል። የናንተን አላውቅም እንጅ አንዳንዴ ይህ አባባል ስድ ፍካሬ ሆኖ አገኘዋለሁ። ግለሰቦች እራሳቸውን ብቻ የሚመለከት የሕይወት ምርጫ ቢያደርጉ የሚጠቅሙትም የሚጎዱትም ያው ራሳቸውን ብቻ ስለሆነ ለዚህ ዓይነቱ ምርጫ ቁብ ሊኖረን አይገባም። ከግለሰብ አልፎ ማሕበረሰብንና ሀገራዊ እንቅስቃሴን በሚነካ ጉዳይ ላይ የሚደረግ ውሳኔ ግን ጉዳያችን ይሆናል።

ከዚህ አንጻር የሕዝብን አመኔታና አደራ የተቀበሉ መሪዎች የሚያደርጉት ውሳኔ የተከታዮቻቸውን ፍላጎትና ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት አያከራክረንም። ግልጽነትና ተጠያቂነት መመሪያዎቻችን ይሆናሉ ብለው ምህላ ፈጽመውልናልና። “ሠላማዊ ወይንም ትጥቅ” በሚል ዓቢይ ጥያቄ ላይ አንድ ወይንም ሁለት ሰዎች ሆነው ውሳኔ ካደረጉ በኋላ የይስሙላ ወረቀት በትነው “ኑ ተከተሉን!” ቢሉ ለሕብረተሰቡ ያላቸውን ንቀት ከማንጸባረቅ በስተቀር ሌላ የሚያመላክተው ነገር የለም። የሀይሉ ሻውል ችግር ይህ ነበር፤ ከልክ በላይ ወጠርከው አትበሉኝና መለስ ዜናዊና ሥዩም መሥፍን ከሱዳን ጋር ያደረጉት ስምምነትም ከዚህ አሠራር ብዙ የተለዬ አይደለም።

እንዲመራኝ የምመኘው ሰው፤ ይልቁንም ደግሞ ድጋፌን የሚሻ ፖለቲከኛ በራዕይ ጥራት፤ በሀቀኝነት፤ በመልካም ስነምግባርና በታማኝነት ባህርዮች የታነጸ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ከዕብሪትና ከመሠሪ ጠባዮች የጸዳ እንዲሆን እፈልጋለሁ። ባስቀመጥሁት ቦታ እንዳገኘው እፈልጋለሁ። ዛሬ እዚህ ነገ እዚያ የሚሉ ሰዎች የምይዘውንና የምጨብጠውን ያሳጡኛልና ቀልቤ አይቀበላቸውም።

አንደኛው የግንቦት 7 መሪ “ሠላማዊ ትግል ከንቱ ነው” ከሚለው ድምዳሜ ላይ የደረሱት እስር ቤት እያሉ እንደነበር ሰምተናል። ይህ ከሆነ ደግሞ በሰላማዊ ትግል ከሚያምነው የቅንጅት አመራር ጋር በአሜሪካን አገር መድረክ መቋደስ አልነበረባቸውም። የጉዞ ፕሮግራሙ መገባደጃ ድረስ ይህን ያህል ግዙፍ ምስጢር ከትግል ጓዶች ደብቆ ማቆየት መልካም የማኔጅመንትና የወዳጅነት ባህርይ አይነበብበትም።

የመሪዎች ባሕርይ ሊቆረቁረን ይገባል ወይ?
ፈረንጆቹ በጣም ሊቆረቁረን ይገባል ይላሉ። መሪ ልሁን ብሎ የሚነሳን ሰው ከነአስተዳደጉ፤ ከነመሠረታዊ ዕምነቶቹ፤ ከነታሪከ ምግባሩ አበጥሮ ማወቅ ወደፊት ሊከሰት ከሚችል አደጋና ፀፀት ይሰውራል - ሙሉበሙሉ ባይሆንም በጅጉ ይሰውራል። ለነገሩ ይህ ብልህነት የፈረንጆች ብቻ አይደለም። ያገሬ ሰው በሲራራ ነጋዴነት አብሮት የሚዘምትን ሰው እንኳ በቅጡ ካላጠናው ከቤቱ አይወጣም። ይችን ያህል ብልህነት እንዴት አጣን?

ለመሪነት የምናጫቸውን ሰዎች በቅጡ መመርመር ነውር የለውምና ይህን ለማድረግ ወኔው ሊኖረን ይገባል። ይህን ሳናደርግ እየቀረን ስንት ጊዜ እንደተበለጥን የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ሞኝን እባብ የነከሰው ሁለቴ ነው ይባላል። አንዴ እባብ ምን እንደሆነ ሳያውቅ አንዴ ደግሞ ከልምዱ ባለመማሩ።

ሁለቱ ተጻራሪ ሀሳቦች ጎን ለጎን የመሄድ ዕድላቸውስ?
ብዙ አይመስለኝም። ግንቦት 7 ንቅናቄውን ከማወጁ በፊትና በኋላ በአባልነት ለመመልመል ሲባጅ የከረመው በሰላማዊ ትግል ዙሪያ የተሰባሰቡትን የቀድሞውን ቅንጅት ያሁኑን የአንድነት ፓርቲ ደጋፊዎች ነው። እዚህም ላይ ትንሺ መሰሪነት ይታየኛል። ባንድ በኩል ለአንድነት መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ እያለ የትብብር ዘንባባ ይዘረጋል። በሌላ በኩል ደግሞ “ሠላማዊ ትግል በተባለው ርዕዮት ቀመስ ትብትብ የታነቀ ትግል” (አንዳርጋቸው ጽጌ) ማካሄድ ፋይዳ ቢስ ነው እያለ የሚሊዮኖችን ዕምነት ያንኳስሳል።

የ1997ቱ የዴሞክራሲ መስኮት ገርበብ ብሎ ከመከፈቱ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላ በነበረው የፖለቲካ መልክዓ ምድር ውስጥ ሕዝብን ማደራጀትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማብቃት ይቻላል ብለው የታገሉ ሰዎች ዛሬ ምን ሀሳባቸውን ሊያስለውጣቸው እንደሚችል አይገባኝም። የኢሕአዴግ ባሕርይ ትናንትም ዛሬም አንድ ነው። በጎሳ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ የሚያራምድ፤ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ በሽታ የተጠናወተው፤ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን የሚረግጥ መንግሥት ነው።

ይህን ሁሉ እያወቅን ነው ሥርዓቱን በሠላማዊ ትግል መለወጥ እንችላለን ብለን የተነሳነው። የ97ቱ የዴሞክራሲ ቀዳዳ የተከፈተው ሕዝብ፤ ፓርቲዎች፤ ነጻው ፕሬስና ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በኢሕአዴግ ላይ ባሳደሩት ተጽዕኖ ነበር። ኢሕአዴግ የተከፈተውን ቀዳዳ ዘግቶ ለማቆየት የሚያስችል አቅምና ምቹ የፖለቲካ ምልክአ ምድር እንደሌለው ማመን አለብን። ሕብረተሰቡ መሀል የሰፈነ የሚመስለው ዝምታ አንድ የፖለቲካ ወይንም የኤኮኖሚ ቀውስ ሲፈጠር የሚለወጥ ነው። እየተደራጀና እያደራጀ በሕዝብ መሀል የሚቆይ ፓርቲ መኖሩ ለቀውጢዋ ቀን ያስፈልጋል።

የትጥቅ ትግል ከማይመረጥበት ምክንያቶች
የትጥቅ ትግል ኮሎኒያሊስቶችንና አምባገነኖችን ለማስወገድ በአማራጭነት ያገለገለው ዓለም በሁለት የፖለቲካ ማዕዘኖች በተከፈልችበት ዘመን ነበር። ለዚያውም ቢሆን አንድን አምባገነን በሌላ አምባገነን ከመተካት ያለፈ ፋይዳ አልነበረውም። ፋይዳ አስገኝቶ ከሆነም ከስንት አንድ ነውና ጂኦ-ፖለቲካው በተለወጠበት ባሁኑ ዘመን እንዳማራጭ መታየቱ ብልህነት ይጎድለዋል።

ሌላም አለ። ጎረቤት አገሮች መጠለያ መስጠት በማይፈልጉበት ዘመን፤ ከራስ ፀጉር የበዛ ሰላይ በከተማና በገጠር ነዋሪው መሀል ተሰግስጎ ባለበት ጊዜ፤ እልቆ መሳፍርት ያለው፤ በዘመናዊ መሣሪያና በሳተላይት መገናኛ የታጠቀ ሠራዊት በሚርመሰበስበት ሁኔታ፤ ምዕራባውያንና የቻይና መንግሥት እሹሩሩ የሚሉት ታዛዥ መንግሥት በነገሠበት ሁኔታ ለትጥቅ ትግል ምቹ አየር ያለ አይመስለኝም። እነዚህ የማያመቹ ሁኔታዎች የሚለወጡት መንግሥትን መውጫ ቀዳዳ የሚያሳጡ ኤኮኖሚያዊ፤ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲገኑ ነው። ያኔ የፖለቲካው ሜዳ የለወጣል።

ሳላነሳ ማለፍ የማልፈልገው ሌላ ነገርም አለ። በትክክል ገብቶኝ ከሆነ ግንቦት 7 የትጥቅንም የሠላማዊ መንገድንም የሚከተሉ ፓርቲዎችን አስተባብሬ ኢሕአዴግን አስወግዳለሁ የሚል ዓላማ ያለው ይመስለኛል። የትጥቅ ትግል ያካሂዳሉ ከሚባሉት መሀል ደግሞ ኦነግና ኦብነግ ሳይኖሩበት አይቀርም። ታዲያ እነዚህ ሁለት ድርጅቶች በኢትዮጵያ አንድነት የማያምኑ መሆናቸው ሲታወቅ ከነርሱ ጋር ማሕበር መጠጣቱ ለምን ግብ ነው? ኤኤፍዲ በተመሳሳይ ዓላማ ሲቋቋም ሁለቱን ድርጅቶች ወደ መሃል ማምጣት ይቻላል በሚል ታሳቢ እንደነበር ትዝ ይለኛል። የሁለት ዓመት ዕድል ተሰጥቷቸው ካቋማቸው ትንሽ እንኳ ፍንክች የማለት አዝማሚያ አለማሳየታቸው እንድንጠረጥራቸው አያደርገንም?

ይህንኑ ክርክር ልቀጥልበትና፤ የኢሕአዴግ መንግሥት በግንቦት 7ም በኦነግም በኦብነግም የትጥቅ ትግል (በአመጽ) ይወገድ እንበል። አመጹ በሚያስከትለው ትርምስ ውስጥ ኦነግና ኦብነግ ለዓመታት ሲያልሙ የነበረውን የመገንጠል ሀሳብ ቢያውጁ ማን ያቆማቸዋል? ይህ ዓይነቱ ትግል በሚፈጥረው ቀውጢ ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያስከብር የተማከለ ሠራዊ እንደማይኖር ከወዲሁ መገመት አያዳግትም።

ከሁለት ገጽ በላይ ላለመጻፍ ለራሴ የገባሁትን ቃል ስላፈረስኩ ይቅርታ በመጠየቅ እዚሁ ላይ አቆማለሁ። አይደግመኝም።

Kuchiye@gmail.com

No comments: