Saturday, September 20, 2008

"አንነጋገር? ... አንደማመጥ?"

ያለንበትን ዘመንና የገባንበትን የፖለቲካ አጣብቂኝ በቅጡ ያጤነ ሰው ይህን ዓይነት ጥያቄ ያነሳል ብዬ ማመን ያስቸግረኛል።

ባለፈው ሳምንት “አዲስ ሬዲዮ” ከአቶ ገብሩ አሥራት ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ያዳመጥኩት በጥሞና ነበር። የፕሮግራሙ አዘጋጅ ያነሳቸው ጥታቄዎች መሠረታዊና በሳል ሲሆኑ አቶ ገብሩም ዋዘኛ የፖለቲካ ሰው አለመሆናቸውን አመላክተዋል ።

ያስደነገጠኝ ነገር ቢሆን ፕሮግሙ ፍፃሜ ላይ በአዘጋጁ ላይ የተሰነዘርው የስልክ ዘለፋ ነው። “ትናንት ከመለስ ዜናዊ ጋር ሆኖ አገር ያስገነጠለ፤ የጎሳ ፓርቲ ያቋቋመ ... ወዘተ እንዴት በፕሮግራምህ ላይ ታቀርባለህ? እንዴትስ ብለህ ሴፕቴምበር 20 ለገብሩ አሥራት የተጠራውን ሕዝባዊ ስብሰባ ታስተዋውቃለህ?” የሚሉ ዓይነት ነበሩ። ይህ ቀሊል አመለካከት በአብዛኛው ሕብረተሰብ ውስጥ እንደማይንጸባረቅ አውቃለሁ። አንዳንድ ሬዲዮ ጣቢያዎች ሥር ተለጥፈው ጉሮሯቸው እስኪነቃ ያንኑ ዜማ መልሰው መልሰው የሚጫወቱት የተወሰኑ ሰዎች ናቸው።

ጎበዝ! “ፖለቲካና ዲፕሎማሲ መንደርደሪያቸውም መደምደሚያቸውም ንግግር ነው። በፖለቲካ ውስጥ ዘላቂ ጥቅም እንጅ ዘላቂ ጠላት የለም” የሚሉትን ብሂሎች ስንት ጊዜ እንደጠቀስኳቸው አላስታውስም። ብሉይ በሐዲስ ኪዳን እንደታደሰ ያልሰሙ ሰዎች ዓይን ያጠፋውን ዓይኑን በማጥፋት፤ የገደለውን በመግደል ካልቀጡ በስተቀር ስርየት የተፈጸመ አይመስላቸውም። ይህ ታዲያ ወደፊት እንዳንራመድ ቀፍድዶ የያዘን አስተሳሰብና ለምንገኝበትም የፖለቲካ አጣብቂኝ ዋነኛው መነሾ ነው። የኛ አገር ብቻ ሳይሆን ኋላቀር በሚባሉ ሀገሮች ሁሉ የተንሰራፋ ነቀርሳ፡፡

ያለፈውን ሰላሳና አርባ ዓመት ታሪካችንን መለስ ብለን ብንቃኝ ብዙ መማር እንችላለን። የአጼ መንግሥት ባንድ በኩል፤ ጀብሀና ሻዕቢያ በሌላ በኩል ተደራድረው ለመስማማት ባለመቻላቸው በየጦር ሜዳው ሺዎች ረገፉ። ባንድ የፖለቲካ ርዕዮት ውስጥ የታቀፉት ኢሕአፓና መኢሶን በታክቲካዊ ልዩነቶቻቸው ላይ ለመወያየት እንኳ ባለመፈለጋቸው የብዙሀን ደም በከንቱ ፈሰሰ፤ እነሱም ድብዛቸው ጠፋ። ደርግም ንግግርን እንደሺንፈት ይቆጥር ነበርና በግትርነት ያካሄደው ውጊያ ለመቶ ሺዎች ህይዎት ማለፍ ምክንያት ሆነ። መለስ ዜናዊና ኢሳይያስ አፈወርቂ ሺምግልናን አሻፈረን ብለው ባካሄዱት ጦርነት እስከ መቶ አርባ ሺህ የሚደርስ ውድ ሕይዎት ጠፋ። የ2005 ምርጫ ያስከተለውን ውዝግብ ለመፍታት ዓለም-አቀፍ ሺማግሌዎች ዜናዊንና ተቃዋሚውን ወገን አነጋግረው ለማስማማት ያደረጉት ጥረት በምቢተኝነት በመክሸፉ የንጹሀን ደም ያለዋዛ ፈሰሰ፤ በሕዝቦች መሀከል አደገኛ ቁርሾ ተዘራ፤ ሕዝባችንም ይህ ነው ለማይባል የአፈና ዘመን ተዳረገ። ብዙ ተስፋ የተጣለበት የቅንጅት እንቅስቃሴ ጉዳት ሊደርስበት የቻለው በመሪዎቹ መሀከል የተፈጠረውን አልባሌ ልዩነት በንግግር ለመፍታት በጎ ፈቃድ ባለመታየቱ እንደነበር ሳላነሳው የማላልፈው ጉዳይ ነው።

በፈረንጆቹ አባባል ታንጎ ለመደነስ የሁለት ሰዎችን ፈቃደኝነትና የጋለ ስሜትን የጠይቃል። ለዚህ ነው ይህ ጥፋተኛ ነበር ይኸኛው ደግሞ አልሚ ነበር ወደሚለው ፍርድ ውስጥ ልገባ ያልፈቀድሁት። ቁምነገሩ ባለፉት አርባ ዓመታት ውስጥ የፖለቲካ ችግሮቻችንን እንደሠለጠነ ህዝብ በንግግር የፈታንበት ዘመን እንዳልነበረ ለማመላከትና የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ እንዲሆን ለማሳሰብ ነው።

አዲስ ሬዲዮ ከገብሩ አሥራት ጋር ወዳደረገው ቃለ-መጠይቅ ልመለስ። አቅራቢው አበበ በለው የተዋጣለት ጋዜጠኛ እየሆነ መምጣቱ ልቤን ያረካዋል። አቶ ገብሩን ሲጋብዝ ትክክለኛ የጋዜጠኛ ሥራውን አከናወነ። ሳይጋብዝ ቀርቶ የወቀሳ ናዳ ቢደርስበት ኖሮ ብዕሬን ባላነሳሁለት ነበርና እሰዬው! እንኳንስ በጋዜጠኝነት ቃልኪዳንህ ተገኘህ እለዋለሁ። ጥያቄውው በሳል መልሱም ጉጉት የሚፈጥር ስለነበር እኒህ ሰው ስላገራቸው ያላቸውን አመለካከት ይበልጥ ለማወቅ በመስከረም 20ው ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወስኛለሁ።

በቃለ-መጠይቁ ከአቶ ገብሩ አሥራት እንደበት የሰማኋቸው “አገራችን በከፋ አደጋ ላይ ትገኛለች! ያለው አስተዳደር ኢዴሞክራሲያዊ ነውና ተባብረን ደሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዘርጋ! 80 ሚሊዮን ሕዝብ ባሕር በር የማግኘት ሕጋዊና ፖለቲካዊ መብት አለው!” የሚሉ ነበሩ። እነዚህ ለጆሮዬ ሙዚቃ ካልሆኑ የትኞቹ ሊሆኑ ነው? ስልክ ደዋዮቹን ያስከፋቸው የትኛው አባባል እንደሆነ ይገባችኋል?

ስዬ አብርሀ፤ ገብሩ አሥራትና ሌሎችም የቀድሞ ሕውሀት አመራር አባላት ባደረጉት ስህተት ተጸጽተው በኢትዮጵያዊነት ጸንተው ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር በጋራ ለመታገል እስከቀረቡ ድረስ ያላንዳች ማመንታት እቅፋችን ውስጥ ልናስገባቸው ያስፈልጋል። አንደኛው ዓቢይ የፖለቲካ ፈተናችን የወዳጅ ክበባችንን ማስፋት ነው። በተለይ ደግሞ በሥልጡን ፖለቲካና በሠላማዊ ትግል የምናምን ወገኖች እገሌን እናናጋግራለን እገሌን አናነጋግርም፤ እገሌን እንሰማለን እገሌን አንሰማም በሚል ቅሌት ውስጥ መታዬት የለብንም። ይህ ጠባይ መሳቁያና መሳለቂያ ከማድረግ አልፎ ለሀገርና ለወገን እንዳንደርስ ጠፍሮ የሚይዝ ሠንሰለት ነውና ልንበጥሰው ይገባል።

ባለፈው አርባ ዓመት በብዙ ጦርነት፤ በተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋና በደካማ አስተዳደር የደቀቀች አገር ጀርባዋ ሌላ የጦርነት ዑደት ሊሸከም ይችላል ብሎ መገመት ያስቸግራል።

ለዚህ ነው አዲሱ መንገዳችን የንግግርና የድርድር መሆን ያለበት። ለዚህም ነው ያዲሲቱ ኢትዮጵያ ልጆች ያገራቸውን ጉዳይ በደመ-ነፍስ ሳይሆን በደመ-በሳልነት መመልከት ያለባቸው። ዘመኑ የንግግር የመደማመጥና የእርቅ ስለሆነ በዚህ ጎዳና ዘና ብለን ለመጓዝ የሚያስችለንን ዕውቀትና ዘዴ ለመካን እንሯሯጥ እላለሁ።

እንዴ! ንግግርና መደማመጥማ የጨዋ ወግ ነው!

Kuchiye@gmail.com
የግርጌ ማስታዎሻ። ኑዛዜው አስፈላጊ እንዳልሆነ ባውቅም ከአቶ ገብሩም ከፓርቲያቸውም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለኝ ይታወቅ

No comments: