Saturday, September 20, 2008

“ፊታውራሪ ተክለሀዋርያት ተክለማርያም - ኦቶባዮግራፊ”
የመጽሐፍ ግምገማ


የዘንድሮው በጋ በሥነ ጽሑፍ ረገድ ፍጹም ለጋስ ነበር ለማለት እደፍራለሁ። ሁለት ድንቅ ያማርኛ መጽሕፍት በማግኘቴ እንደታደልኩ ቆጠርኩት። የፊታውራሪ ተክለሀዋርያት “ኦቶ ባዮግራፊ” እና የብላቴን ጌታ መርስዔ ሀዘን “የኢትዮጵያ ታሪክ -ከንግሥት ሳባ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ” ግሩም መዘክሮች ብቻ ሳይሆኑ ባገራችን፤ በሕዝባችን፤ በባህላችንና በታሪካችን ላይ የየራሳችንን ግንዛቤ እንድንይዝ ነፃነት የሚሰጡ ሆነው አገኘኋቸው።

ስለሁለቱም መጻህፍት ባንድ አፍ መመስከር በሁለቱም ላይ ወንጀል መፈጸም ስለሚሆንብኝ በዛሬው አቅርቦቴ የተክሌ ኦቶባዮግራፊ ያሳደረብኝን ስሜት አካፍላችኋለሁ።

አስተዳደግ
ተክለሀዋርያት የተወለዱት በ1874-1876 አካባቢ ተጉለት ውስጥ ነው። እስከ ዘጠኝ ዓመት ዕድሜያቸው በቄስ ትምህርት ቆዩና ወግና ሥርዓት ያጠኑ ዘንድ በአደራ ልጅነት ሀረር ለራስ መኮንን ተሰጡ። በዚያ ዘመን ልጁን በጌታ ቤት ለማሳደግ የቻለ ወላጅ የታደለ ነበር። በኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌላውም። “ሳይደብር” መንደር የተወለደችው ተክሌ “በቤት ላይ ቤት የተሠራበትን” የሀረር ከተማ ስታይና በሱቆቹ ውስጥ የተደረደሩትን ስንትና ስንት ዓይነት የባህር ማዶ ዕቃዎች ስትመለከት ጉድ! አለች፤ ምኞትም ተለኮሰባት።

“ባህር ማዶ የሚባለውስ አገር እነዚህ ሁሉ የውበት ዕቃዎች የሚፈጠሩበት ስንትና ስንት ጥበብ ይገኝበት ይሆን?… እዚያው ድረስ ሄዶ ማየት፤ መፈረጅ፤ መመርመር፤ መዳሰስ የሚቻል ቢሆን እንዴትስ ባስደሰተ ነበር?” አለች።

ተክሌ ብሩህ ጭንቅላት ያላት ብልጣብልጥ “ማቲ” ስለነበረች ራስ መኮንንና ባለቤታቸው ሲወዷት ጊዜ አልፈጀባቸውም። እንደሎሌ ሳይሆን እንደ ልጅ አቀረቧት፤ ትምህርት ቤት አስገቧት። ከሃላፊነታቸው ጋር ተያይዞ በሚመጣ ሃሳብ ሲወጠሩ እንኳ ራስን የምታስቅ ተክሌ ሆና ተገኘች። ባለሟልነታቸው ከመጥበቁ የተነሳ አድዋ ጦርነት ካልዘመትኩ ብላ ብታለቅስባቸው ራስ መኮንን ሊጨክኑ አልቻሉም። “ግዴለም መንገድ ለመንገድ ያጨውተኛል ይዝመት” አሉ። አዎን ተክሌ ለዘመቻ ክብር በመብቃቷ ጓደኞቿ እስኪቀኑባት ድረስ ፈነደቀች። የተሸለመችውን መሣሪያ ወልውላ በአሥራ ሁለት ዓመቷ ለወግ በቃች። ግዳይ አታስቆጥር እንጅ እንዳቅሚቲ ከዚያ ያላነሰ ቁምነገር ሠራች።

በተክሌ ብሩህነትና የማወቅ ጉጉት የተማረኩት ራስ መኮንን ተክሌን ባሕር ማዶ ልኮ ለማስተማር ቃል ገቡ። ታዲያ ይህ ቃልኪዳን ተድበስብሶ ይቀራል የሚል ስጋት ያደረባት ተክሌ ራስን መውጫ መግቢያ አሳጥታ በጃንሆይ አፄ ምኒልክ ፈቃድ በአሥራ ሦስት ዓመቷ ሩስያ እንድትሄድ ሆነ። ሩስያ ያኔ የምትተዳደረው በንጉሠ ነገሥት ዛር ኒኮላ 2ኛው ነበር። ኮሚኒዝም ባገሩም አልተፈጠረም።

የመጽሐፉ ጭብጥ

ጽሑፉ በዕውነተኛ የሕይወት ታሪክ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የአንባቢን አመኔታና ቀልብ የመማረክ ኃይል አለው። ገና በህጻንነት ዕድሜ ባለታሪኩ ህሊና ውስጥ የተጠነሰሰው የማወቅና ሕብረተሰብን የመለወጥ ጉጉት ያዳም ዘር ጉጉት ነውና ወዲያውኑ እንጋራዋለን። ይሳካለት ይሆን? የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በማያውቀው አገር ባህልና ዘመናዊ አኗኗር ከተነከረ በኋላ ከቀድሞ ጉጉቱና ከኢትዮጵያዊነቱ ጋር የመመለስ ዕድሉ ምን ያህል ይሆናል? ተምሮ የሚመለስ ቢሆንስ በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን ኋላቀር ስርዎ ምንግሥትና ባህል የመቋቋም አቅም ይኖረዋል? ሥር በሰደደ ጥቅም የተሳሰሩት መሳፍንት፤ ባላባቶች፤ መሀል ሰፋሪዎች፤ ካሕናትና ሸኮች ምን ፈተና ይደቅኑበት ይሆን? ይህንን ሁሉ ለመቋቋም የሚያስችል የህሊና ጽናት፤ ስልትና ትዕግሥት ይኖረውስ ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች መንፈሴ ውስጥ የተደረደሩት ከመነሻው ነበር። የተዋጣላት መጽሐፍ እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችንና ስጋቶችን ባንባቢ ዓዕምሮ ውስጥ የመጫር ችሎታ አለው።

ከሥነ ጽሑፍ አኳያ
ይህ መጽሐፍ አንጸባራቂ የሥነጽሑፍ እሴቶች አሉት። ትረካው በአጫጭር ዓረፍተነገሮች የተገነባ ስለሆነ አንባቢን ትንፋሽ በሚያስቆርጥ ሀተታ ውስጥ አያንከራትትም። በጥንቃቄ የተመረጡ የለት-ተለት ቃላት ሕብረት ጽንሰ ሀሳቦችንም ሆነ ትረካዎችን የቱን ያህል እንደሚያሳምሩ በውል ያየሁት በዚህ መጽሐፍ ነው።

ፊታውራሪ ተወለዱበትን አጥቢያ፤ የህዝቡን አኗኗር፤ የራስ መኮንንን ችሎት፤ የመቀሌን ያምባላጌንና የአድዋን ጦርነቶች፤ እንዲሁም በልጅ እያሱና በተፈሪ መኰንን መሀከል የነበረውን የሥልጣን ሽኩቻ ፤ የሩስያ ቤተሰቦቻቸውን የተንጣለለና የረቀቀ አኗኗር፤ የኑሮ ፈተናዎቻቸውንና ገጠመኞቻቸውን የሚገልጹት ጨርቁን በጣለ ግልጽነት ነው። ቀልዳቸውና ያጻጻፍ ዘይቤያቸው የሚያስቅበት ጊዜ ብዙ ነው። ከሌሊቱ 8 ሰዓት እንደዕብድ ብቻየን የተንከተከትኩትን ቀን አልረሳውም። ታዲያ ልብ ያላለ ሰው አንዳንዱን ወዛም ቀልድ ሊስተው ይችላል።

በፊታውራሪ አገላለጽና የትንታኔ ዘይቤ ውስጥ ደግሞና ደጋግሞ የሚታይ ነገርም አለ። እኒህ ፀሐፊ የጣኦት ያህል የሚታዩትን የነቶልስቶይን፤ የነፑሽኪንን፤ የነሸክስፔርንና የሌሎችንም ሥራዎች በግላቸውና በሩሲያ አካዳሚ ውስጥ አንጥረውና አበጥረው ያነበቡ ለመሆናቸው አጻጻፋቸው ይመሰክራል። ስለዚህም ዘይቤያቸው ካብዛኛው ኢትዮጵያዊ ደራሲ የተለየ ሆኖ ታየኝ።

ተክሌ መልክዓ ምድሮችን፤ የታሪክ ክስተቶችን፤ የፖለቲካና ያስተዳደር ገጠመኞችን ሲገልጹ ባንባቢው ሕሊና ውስጥ የሚቀርጹት ሥዕል የሲኒማ ያህል ነው። ያውም ህብረቀለማዊ “ሃይ ዴፊኒሽን” ሲኒማ ያህል። የጸሐፊው ተክሌና የኔ ገጸባህርይ በብዕር ኃይል አንድ ሆኑ። ሳይደብር ምንጃር ከተክሌ ጋር ፊደል ቆጠርኩ፤ ዳዊት ደገምሁ፤ ስቦርቅ አደግሁ። በራስ መኮንን አደባባይ እድሌን አስተካከልሁ። አድዋ ላይ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ፤ የመስዋዕትነትን ክብር፤ የኋላቀርነትን ጣጣ፤ የየዋህነትን መዘዝ፤ የክህደትን አስጸያፊ መልክ አስተዋልሁ። ሩሲያ በተክሌ “አያት” ቢብሊዮቴክ ውስጥ የተደረደሩትን መጻህፍት ከተክሌ ጋር ሆኜ አስጨነቅኋቸው፤ የሥልጣኔን ምስጢር ውለዱ አልኳቸው። ያገሬን ድህነትና ኋላቀርነት አንጀቴን እስኪያመኝ ድረስ ተቀበልሁት። በትጋት ተምሬ በቶሎ ላገሬ እንድደርስላት ከተክሌ ጋር ምህላየን አደስኩ።

የተክለሀዋርያት ፈተናዎች
ተክለሀዋርያት ኢትዮጵያ ከተመልሱ በኋላ የገጠማቸው ፈተናና ያለፉበት መንገድ አንባቢን ሰቀቀን ውስጥ የሚጥል ነው። ያስጨንቃል፤ ያስቆጣል፤ ያስተክዛል፤ ተስፋ ይሰጣል፤ እንደገና ደግሞ ተስፋ ያጨልማል። ሥልጣኔን ለማምጣት በሚተጉና የቀድሞውን ሙጥኝ በሚሉ መሀከል የሚካሄደው ጦርነት፤ ሴራ፤ ሺወዳ፤ እጅግ የበዛ ነበር። የተክሌ ጨቅላ መንፈስ በሚኒልክ የሥልጣኔ መውደድ ተማርኮ ነበር። ከሩስያ እንደተመለሱ ምኒልክ ስለሞቱ ለውጥ የማምጣት ተስፋቸውን መጀመሪያ በልጅ እያሱ ላይ፤ የልጅ እያሱ ነገር እንዳልሆነ ሲሆን በተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለ ሥላሴ) ላይ አሳረፉ።

ተክሌ ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣትና ከጥቃት ለመጠበቅ የሚጠፋ ጊዜ ሊኖር አይገባም፤ በሀቅና በጥድፊያ መሥራት አለብን ባይ ነበሩ። አፄ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ ይዘው የተነሱትን የለውጥ ተስፋ ለከንቱ ውዳሴና ለሥልጣን መቆያ ዳረጎት እያደረጉት መጡ። የተክለሀዋርያት ሀቀኝነትና ድፍረት ለቤተመንግሥቱና ለሥርዓቱ አልመች ስላለ ውለታ በሠሩላቸው ንጉሥ ታሠሩ በኋላም የግዞት ያህል በሀረር ሂርና እርሻቸው ላይ ኖረው አለፉ።

ኦቶ ባዮግራፊ መጻፍ ባልተለመደበትና ምናልባትም ስለራስ መመስከር እንደጉራ በሚቆጠርበት አገር የቀድሞዋን ኢትዮጵያ የምንመለከትበት መስኮት ስለከፈቱልን የፊታውራሪ ተክለሀዋርያትና የሳታሚ ልጆቻቸው ባለውለታ ነን። መጽሐፉ በቴፕ ቢቀረጽ ለብዙዎች የደስታ ምንጭ እንደሚሆን አይጠረጠርም። ለዶኪመንታሪና ለፊልምም በጣሙን የተመቼ ነውና እስቲ እንነጋገርበት። ወዳጆቼ! ይህ መጽሐፍ ከቤታችሁ መጥፋት የሌለበትና ለወዳጅ እንኳ የማይዋስ ነው።

የግርጌ ማስታወሻ
አንድ ሰው ስለራሱ ሲተርክ ያለፈባቸውን ዘመናት የታሪክና የባህል ጭብጦች መነካካቱ ግድ ነውና መጽሐፉ የሱ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የትውልድም ታሪክ ይሆናል። ስለዚህ ፖለቲከኛውም፤ አስተዳዳሪውም፤ ነጋዴውም፤ ገበሬውም፤ ደራሲውም፤ ተዋናዩም ኦቶባዮግራፊ የመጻፍ ባህል እንዲያደብሩ ተገቢ ነው። “አይ እኔ ምን ታሪክ አለኝና?” በሚል ራስን ዝቅ በሚያደርግ ባህል ታስሮ ኦቶባዮግራፊ ከመጻፍ መቆጠብ የትውልድ ታሪክ ተቀርጾ እንዳይተላለፍ የሚያደርግ ዓይነት ወንጀል ይመስለኛልና በተለይ ዕድሜ መገባደጃ ላይ ያላችሁ ተነቃቁ እላለሁ።

kuchiye@gmail.com

No comments: