Friday, June 05, 2009


"ይድረስ ለውድ ብርቱካን!"
ቃሊቲ እስር ቤት - አዲስ አበባ


“ታውቅ ይሆን?” እያልኩ አወጣና አወርዳለሁ። “የስንቱን ህሊና እንደነካች ታውቀው ይሆን?” እላለሁ።

የሰሞኗ ጀንበር የምትጠልቀው የሁለተኛ ልጄን መወለድ ሳሰላስል ነው። ታዲያ ከየት መጣ የማልለው ጭንቀት በድንገት ይወረኛል። ጭንቀቱ ስለልጆቼ እንጅ ስለኔ እንዳይመስልሺ። “እኔ የማውቃትንና ያደግኩባትን ኢትዮጵያ፤ በማይነጥፍ የፍቅር እስተንፋስ ኮትኩቶ ያሳደገኝን ቀዬ፤ ይሰማኝ የነበረውን ልበ-ሙሉነትና ብሩህ ተስፋ፤ በበቂ የማይወሳለትን የወገኔን ጨዋነትና የመቻቻል ባህል.....ልጆቼ የነዚህ ቅርሶች ባለቤት የመሆን ዕድል ይገጥማቸው ይሆን?” እያልኩ ነው የምጨነቀው።

ከአጉል ውዳሴ አይቆጠርብኝ እንጅ ምንኛ ስሜቴን እንደነካሺው ላሳውቅሺ እፈልጋለሁ። ከቃሊቲ እሥር ቤት በጥር ወር 2006 ገደማ የፃፍሺውን ደብዳቤና አሁን በታህሳስ 2008 እንደገና ወደ እስር ሊወረውሩሺ ሲዘጋጁ “ቃሌ!” በሚል ርዕስ ለሕዝብሺ የሰጠሺውን ምስክርነት ደጋግሜ አነባቸውና ስሜቴ ሲታደስ አየዋለሁ። አልፎ አልፎም ይሁን እንጂ ዓለማችን ጠንካራ መንፈስ ኖሯቸው የተስፋ ራዕይ በሚናኙ ሰዎች መታደሏን አስታውሼ እጽናናለሁ። ስለጠንካራ መንፈስሺና ስለ ተስፋ ሰጭነትሺ ከልብ አመሰግንሻለሁ።

ውድ ብርቱካን!
ቀይ ሺብርና ነጭ ሺብር የወላጆቻችንን ቅስም ሰብረው ለስደት ኑሮ ዳረጓቸው። አሁን ደግሞ ሕዝባችንን በጎሳና በሀይማኖት ለመከፋፈል የሚረጨው መርዝ የምንተነፍሰውን አየር እየበከለው ይገኛል። ለዚህ ነው ያሁኑም ትውልድ ስደተኛ እየሆነ የመጣው። አየሺ! ያምባገነኖች ተግባር ርኩስ ነው የሚባለው ተቀናቃኞቻቸውን በመፍጀታቸውና በማፈናቸው ብቻ አይደለም። ከዚያ ባላነሰ የሚጎዱን መጭው ትውልድ የተስፋ ባለቤት እንዳይሆን በሚያካሂዱት የሥነ-ልቦና ጦርነት ነው።

“ዴሞክራሲንና በሥነ-ምግባር የታነጹ መሪዎችን መሻት መብታችን ነው!” ማለትን ካቆምን፤ ተፈጥሯዊና ሕገመንግሥታዊ መብታችንን ከጃችን ሊመነጭቁ ሲመጡ “ወግዱ አናስነካም!” ማለትን ካልለመድን ያኔ ነው የሺንፈትም ሺንፈት የሚሆንብን። ለዚህም ነው ያንች “ወግዱ!” እና “መብቴን አላስነካም!” ለሁላችን ምሣሌ የሆነው።

ኢሕአዴግ ሊያሳምነን የሚጥረው ኢትዮጵያ ከዚህ የተሻለች መሆን እንደማትችል ነው። የተሻለ ዴሞክራሲ፤ የተሻለ ፍትህ፤ የተሻለ አስተዳደር ሊኖር እንደማይችል። የሚመራንን ፓርቲ ስንመርጥና ለዴሞክራሲ ዝግጁ መሆናችንን ስናስመሰክር የዴሞክራሲን ጎዳና ፈጽሞ ይዘጋዋል። የጎሣ ፖለቲካ እንዳላመቸው ሲረዳ የሀይማኖትና ሌሎች ልዩነቶችን ያሰፋፋል። ይሁን እንጅ ኢሕአዴግ ራሱ የማይስተው አንድ ዕውነታ አለ። የሚቆጣጠራቸውን የእርሻ መሬቶች፤ የፋይናስና የንግድ ድርጅቶች፤ ትልቅ ደመወዝ ከፋይነቱንና ወታደራዊ ኃይሉን የጭቆናና የማባበያ መሣሪያ ባያደርግ ኖሮ ላንድ ጀንበር ሥልጣን ላይ እንደማይቆይ ያውቃል። በሕዝባዊ ፍቅር ተከልሎ በሁለት እግሩ የቆመ መንግሥት እንዳልሆነ ያውቀዋል። ባለሥልጣኑም ካድሬውም ሠራዊቱም በውስጣቸው ይህን ያውቃሉ።

ውድ ብርቱካን!
ኢሕአዴግ በጥፋት ጎዳና መጓዙን አቁሞ የሕዝብና ለሕዝብ የሚያደርገውን ጎዳና ቢመርጥ የሁላችንም ምኞት ነው። የኛው መንገድ የአንድነት የዴሞክራሲ የመብት የዕኩልነትና የዕርቅ ስለሆነ በፍቅርና በተስፋ ተሞልቷል። ለሰው ልጅ ከተስፋ የሚበልጥ ቁምነገር የለምና ተስፋን ምርኩዛችን እስካደረግን የነገው ሕይወታችን ከዛሬውው የተሻለ እንደሚሆን አንጠራጠርም።

የተስፋን የአንድነትንና የጥንካሬን ካባ ስላላብሺን ለውለታሺ መጠን የለውም። በቅርቡ ከእስር ወጥተሺ የጀመርሺውን ያዲስ ትውልድ አደራ እንድትወጭ፤ ያዲሲቷን ኢትዮጵያ ጉዞ አብረሺን እንድትጓዥ እንጸልያለን። የኔዎቹ ሁለቱ እንዲሁም ያንችዋ “ሄሌ” እጅግ መልካም የሆነች ኢትዮጵያ ትኖራቸዋለች።
kuchiye@gmail.com

No comments: