Friday, May 29, 2009

"መሬት የመቸብቸቡ ጉዳይ! "

ችስታ የመታቸው አገሮች ሰፋፊ መሬታቸውን ለውጭ መንግሥታት በገፍ የመቸብቸባቸው ፈሊጥ በዓለም መድረኮች አነጋጋሪ ሆኗል። በኛው አካባቢም ብዙ ንትርክና ቁጣ እንደጫረ ተረዳሁና ጉዳዩን መመርመር ጀመርኩ። ሳያጣሩ ወሬ ሳያነቡ መምሬ መሆን አጉል ነውና በመጠኑም ቢሆን አንብቤ ያገኘሁትን ላካፍላችሁ።

ሳኡዲ፤ ኤሚሬት፤ ኳታር፤ ኩዌት፤ ግብጽ፤ ሊቢያ፤ ቻይና፤ ደቡብ ኰርያና የመሳሰሉትን አገሮች የእህል ዋጋ ሰማይ እየነካ መሄዱ የምግብ ሴኪውሪቲ እያሳጣቸው ነው። ባዮ-ፊውል ለማውጣት ሲሉ ፈረንጆቹ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን እህል መቀነሳቸውም ሼኮቹን ያስደነቀ አይመሰለኝም።

ይሁን እንጅ እንደ ሳኡዲ ያሉትን የናጠጡ ሀብታሞች ያሳሰባቸው ከላይ የተጠቀሰው ብቻ አይደለም። ሳውዲዎች በማይታመን ዋጋም ቢሆን እህል በበረሀ ውስጥ ያመርታሉ። የሳውዲ እርሻዎች ለብሔራዊ ኩራት ምንጭ ሆነው ይቆዩ እንጅ በከርሰ-ምድር ያለውን የውሀ ክምችት ክፉኛ በሟሟጠጥና አካባቢን በመበከል ረገድ ጋውፋህ (የተሲያት እንቅልፍ) የሚነሱ ዓይነት ሆነውባቸዋል። በኢትዮጵያው ኮንትራት የተመረተው ሩዝ በታላቅ ሥነ-ሥርዓት ታጅቦ ለሳኡዲው ንጉሥ ሲቀርብላቸው በፈገግታ የተሞሉት ያለምክንያት አልነበረም። ለምን አይሞሉ? ርስቱ ከወንዝ ባሻገር፤ የተገኘው በነፃ፤ የኤክስፖርት ታክስ አይከፈልበት፤ የሚሟጠጠው የሌላ አገር ውሀ፤ የሚመረዘው የሌላ አገር መሬት።

ከወዲሁ ላስጠንቅቃችሁና የውጭ ኢንቬስትመንት ለዕድገት እጅግ አስፈላጊ ግብአት ነው ከሚሉት ወገን ነኝ። ስለሆነም የመሬቱን ኮንትራት የማየው በ “ጠርጥር” መነጽር ተጋርጄ አይደለም። ለዚህም ነው አዲስ ዓይነት “የጅ-አዙር ቅኝ አገዛዝ” ወዘተ የሚለውን ዝባዝንኬ ክርክር የማልስማማበት። አገርም ግለሰብም የሚፈርሙትን ውል በቅጡ ካሰቡበትና ጥቅማቸውን ለማስከበር በቂ ጥንቃቄ ካደረጉ የጅ-አዙርም የሌላም ዓይነት ቅኝ አገዛዝ ሰለባ አይሆኑም። ደ!

በነገራችን ላይ በመሬት ችብቸባው ንግድ የተሰማራችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሱዳን፤ ዛምቢያ፤ ታንዛኒያ፤ ኮንጐ፤ ሞዛምቢክ፤ ካምቦዲያ፤ ዩክሬን፤ ሰርቢያና የመሳሰሉት ጭምር ናቸው። ሩስያ አውስትራሊያና ብራዚልን የምያካክሉ የዳጎሰ ኤኮኖሚ ያላቸው ሳይቀሩ ከነሳኡዲ ጋር ሽር ጉድ እያሉ ነውና ያዲሱ ዓለም የኢንቬስትመንት ቄንጥ ይህ እንደሆነ እንወቅ። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም ድርሻዋን ለማግኘት ብትሯሯጥ ልንገረም አይገባም - ኢንቬስትመንት ካፒታል እንደሷ የሚያስፈልገው አገር የለምና።

ታዲያ ችግሩ የት ላይ ነው? በጣም ጥሩ ጥያቄ። ችግሩ ያለው መሬት የሚቸበችቡት አገሮች ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በማያውቁ መንግሥታት ሥር የሚተዳደሩ መሆናቸው፤ አኮናታሪዎቹም ተኮናታሪዎቹም ሙስናን ባህል ያደረጉ መሆናቸው፤ የውል ዝርዝሩ ድብቅ መሆኑ፤ ኢንቬስተሩ ያመረተውን እህል ሙልጭ አድርጎ ወዳገሩ ወይንም ወደ ዓለም ገበያ የመውሰድ መብት እንዲኖረው መደረጉ ይገኙበታል። ይህ ብቻ አይደለም! ውሉ ስለከባቢ ዓየር መበከል፤ ስለብሔራዊ የውሀ ቋት መሟጠጥ፤ ስለነዋሪው ሕዝብ መፈናቀል ከመጨነቅ ይልቅ የኢንቬስተሩንና የውል ሰጨዎችን ኪስ በማሟሸት ላይ የተጣደፈ ነው የሚሉም ይበዛሉ። እኔ ማነኝና ነው አዋቂዎች የሚሉትን ላስተባብል የምሞክረው? እንቀጥል…

ከኢንቬስተሮቹስ ምን ይጠበቃል? ይህም ሌላ ጥሩ ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያን በሚመለከት ከሳውዲ ኢንቬተሮች ጋር የተፈረመው ውል በምስጢር ስለተያዘ ምን ዝርዝር እንዳለው አይታወቅም። ይህ ነው እንግዲህ ግልጽ ያለመሆን ጣጣ። ኢንቬስተሮቹ የሚሉት የሥራ ዕድል፤ ምርጥ ዘር፤ አዲስ ቴክኖሎጅ፤ ዘመናዊ ማኔጅመንት፤ ትምህርት ቤቶች፤ ክሊኒኮች፤ ይዘን እንመጣለን ነው። ከተጠቀሱት ጥቅሞች ኢትዮጵያ ምን ያህሉን እንዳገኘች የሚያውቅ ሰው ካለ ይንገረንና የትኞቹ ዕውንት የትኞቹ ደግሞ ባዶ ተስፋ እንደሆኑ መለየት እንችላለን።

እስከዚያው ድረስ ግን ከሌሎች አገሮች ያገኘነውን ተመክሮ መሠረት አድርገን መወያየቱ ክፋት የለውም። ሌሎች አገሮች ውስጥ የተቋቋሙ የ “መንግሥት-ለመንግሥት” ወይንም የ “መንግሥት-ግል” የርሻ ኮንትራቶች ብዙ ፋይዳ አሳይተው እንደማያውቁ ያለም ታሪክ ይመሰክራል። ለነገሩ መንግሥት የሚይዘው ነገር የት ቦታ ነው ፈይዶ የሚያውቀው? ባንጻሩ ደግሞ የውጭ የግል ኢንቬስተሮች ካገሬው የግል ኢንቬስተሮች ጋር የሚጀምሯቸው ፕሮጀክቶች ብዙ ውጤት ታይቶባቸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉን በጄ ከሚለው አባዜ እስካልተላቀቀ ድረስ የሳውዲውም ሌሎችም ፕሮጀችቶች ብዙ ዕድሜ እንደማይኖራቸው ከወዲሁ መመስከር ይቻላል።

ወደማጠቃለሉ ላምራ። ከላይ እንደጠቀስኩት የውጭ ባለካፒታሎች በደሀ አገሮች ውስጥ የእርሻ ሥራ ለማስፋፋት መሺቀዳደማቸው የዘመናችን ክስተት ነውና ልናቆመውም ልንሸሸውም አይገባም። ጥያቄው ኢንቬስተሮች ይግቡና አይግቡ ከሚለው ላይ አይደለም - ይህ ብዙ አያከራክርምና። ፍሬ ነገሩ ያለው እንዲህ ያለው ውል ሁለቱንም ወገን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚጠቅም ነው አይደለም ከሚለው ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ የግልጽነት ጥያቄ ወሳኝ ይሆናል። ያገሬው ኢንቬስተር ተሳታፊነት ወሳኝ ይሆናል። ብሔራዊ ጥቅም የማስከበሩ ጉዳይ ወሳኝ ይሆናል። ተገቢው የኤንቫይሮንሜንት ሕግ መውጣቱና ማስከበሪያ መሣሪያዎቹም መደራጀታቸው ወሳኝ ይሆናል። የውጭው ካፒታል የሚንቀሳቀስበት የሕግ ዳር-ድንበር መከለሉ ወሳኝ ይሆናል። ስለሚፈናቀለው ገበሬና በከብት-ርቢ ስለሚተዳደረው ሕዝባችን እጣ-ፈንታ በቅጡ ማሰብ ወሳኝ ይሆናል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የዴሞክራሲ የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት መስፈንን የግድ ይላል።

እነዚህ ሳይሆኑ ቀርተው የመንግሥት ቢሮክራቶች በግብታዊነትም በሌላ ተነሳሺነትም የሚያደርጉት ውሳኔና የሚፈራረሙት ውል የሚያስገኘው ጥፋትና ኪሣራ ነው። በቆቃ ሀይቅና በወንዞቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ሁኔታ አሳዝኖን ከሆነ ይኸኛው ደግሞ ከትውልድ ወደትውልድ የሚተላልፍ የሀዘንም ሀዘን ይሆናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የውሎቹን ዝርዝር የማወቅ መብት አለው።

Kuchiye@gmail.com

----------
(እንግሊዝ ለሚቀናችሁ፡ “The Economist” May 23, 2009 አንብቡ። ብዙውን ያገኘሁት ከዚያ ነው)

No comments: