Wednesday, March 10, 2010

ቢያንስ ዶሮዋን አንሆንም?


ሹም መሆን ብዙ ፈተና አለው ወዳጄ! አንዲት አነስተኛ ወረዳ ውስጥ አስተዳዳሪ ሆኖ የተመረጠ ሰው የህዝቡን ተሳትፎ ለማግኘት ቁርጥ ሀሳብ ያደርጋል። የነጋዴው፤ ያስተማሪው፤ የተማሪው፤ የገበሬው በር አልቀረውም። የሁሉንም አንኳኳ። አንዱን ቀን እግሩ ካንድ ገበሬ ቤት ይጥለውና...


“የዛሬው አመጣጤ አንድ ኮሚቴ ውስጥ በአባልነት እንዲሳተፉልኝ ለመጠዬቅ ነው” ይላል አስተዳዳሪው።

“ታዲያ ምን ገዶኝ ጌታው! ተሳትፎዬን የሚፈለጉት በምን መልክ ነው? የዶሮዋን ወይንስ የበሬውን ዓይነት?” ይመልሳል - ገበሬው።

አስተዳዳሪው በገበሬው ጥያቄ ግራ ተጋባና፤ ደግሞም ገበሬዎች የአግብኦና የተምሳሌት ጨዋታ እንደሚወዱ ያውቅ ነበርና ፍችውን ለማግኘት ጉጉት አደረበት።

“አልገባኝምና እንዲያው ጥቂት ቢያብራሩልኝ” ይለዋል ገበሬውን...መልሱን ለማዳመጥ ትጋቱን አሰባስቦ።

“አይ! ተሳትፎ ማለት ሥጋ ጣል-ጣል እንደተደረገበት የንቁላል ጥብስ ነው...ዶሮዋ ለጥብሱ አስተዋጽኦ ታደርጋለች እንጅ ራሷን አሳልፋ አትሰጥም” በማለት እንቆቅልሹን ፈታለት አያ ገበሬ።

ይችን ጨዋታ ያካፈለኝ አንዱ እጁ ከመጽሐፍ አንዱ ደግሞ ከላፕቶፕ ገበታ ላይ የማይነሳ ሌላው ወዳጄ ነው። ይንግሊንግ ቢራችንን (ይሄኔ እኮ ያሜሪካ ቀዳማዊ ቢራ መሆኑን የማታውቁ ትኖራላችሁ!) ጨብጠን በሌላ ርዕስ ላይ ገራ-ገር ጨዋታ ስንሰልቅ ነው አንቀጹን ያነበበልኝ። አጉል ልማድ አይለቅምና ሀሳቤ እንደገና ወደኛው ጉዳይ አቀና....

ስንቶቻችን ነን የዶሮዋን ያህል አስተዋጽኦ እያደረግን ያለነው? ስንቶችስ ናቸው የበሬውን ያህል ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት የቆረጡ?

“ሠላማዊ ትግል” በሚለው አንቀጽ ውስጥ “ሠላም” የምትለዋ ቃል አዘናጊ ሆና ትታየኛለች - በዚህ ጎራ የሚታገሉ ዜጎችና ቤተሰቦቻቸው ያለችግርና በሠላም ውለው የሚያድሩ ታስመስላለችና። ዕውነቱ ግን ይህ አይደለም። በሙሉም ይሁን በከፊል አዱኛቸውን እርግፍ አርገው የሚጥሩ ሁሉ ችግር ይኖራቸዋል። ፓርቲዎቹስ ቢሆኑ ከየት በመጣ ገንዘብ ነው ከክልል ክልል ተዘዋውረው በምርጫው የሚወዳደሩት? ሕዝቡስ ጋር የሚገናኙት?

በርግጥ ከመንግሥት የሚሰጥ በጀት እንዳለ ሰምቻለሁ። ግን ዘጠኝ ሺህ የኢትዮጵያ ብር የት ታደርሳልች? አባባሌ አገር ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችን መደገፍ የዜግነትና የህሊና ግዴታ አለበት ለማለት ነው። የዚህ ወይንም የዚያ ፓርቲ ደጋፊ መሆናችን አይደለም ቁምነገሩ። ለሀገራችን ዴሞክራሲንና ሠላምን የምንመኝ እስከሆነ ድረስ ለዚህ ለግንቦት 2002ቱ ምርጫ የሚረዳ አሥርና ሃያ ብር ለሚመስለን ፓርቲ ማዋጣቱ ላይ ነው ቁምነገሩ።

ዶሮዋ ዕንቁላሏን ከቸረች እኛ ከማሕፅናችን ያልወጣው $20 ዶላር ይገደናል? ቢያንስ ዶሮዋን እንሁን!

Can we be the goose?
March 10, 2010
kuchiye@gmail.com

No comments: