Saturday, March 01, 2008

ይድረስ ለአቶ ኃይሉ ሻውል
አሜሪካ
March 1 2008


ቃሊቲ በእስር ሆነህ ለጻፍኩልህ ደብዳቤ እስካሁን መልስ ባላገኝም አንዳችም ቅሬታ አላደረብኝ። አንድም የጤንነትህን ጉዳይ ስለማውቅ ሌላው ደግሞ ከምርጫው ወዲህ የተመሳቀለውን ፖለቲካ ግራ-ከቀኝ አገናዝበህ ያላፊነት ግዴታህን ለመወጣት ፋታ እንደሚያስፈልግህ ስለማምን ነበር።

ይኸው ከተፈታችሁ ስድስት ወር ያህል ሆነ። ታዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችገር እጅጉን እየባሰ፤ የመንግሥት አምባገነንነት ቅጥ እያጣ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሮሮ እየጠና፤ የጦርነት ዳመና በሰሜንና በምሥራቅ እያንዣበበና ሕዝባችን ታይቶ በማይታወቅ የኑሮ ውድነት አለንጋ እየተገረፈ ነው። በዚሁ ላቁም ብየ ነው እንጅ ዝርዝሩ እንኳ እርቆ መሳፍርት የለውም።


ከላይ የዘረዘርኩዋቸው ፈተናዎች ከህመምህ የበለጠ እንቅልፍ እንደሚነሱህ ላንዳፍታም አልጠራጠር። ሕዝብ ለነዚህ ሁሉ ችግሮቸ መታደጊያ ይሆነኛል ብሎ ተስፋ የጣለበትን የቅንጅትን ቤት መልሶ ለማቋቋም በሚደረግ ወሳኝ ጥረት ውስጥ ማንንም ምንንም ሳታስቀድም ትሳተፋለህ ብየ ብጠብቅም የምሳሳት አይመስለኝም። ታዲያ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረን ችግር ለመፍታት ይህን ያህል ጊዜ መፍጀቱ ምን ይባላል? ኬንያ ውስጥ በሁለት ተጻራሪ ፓርቲዎች መሀከል የተከሰተው በደም የተበከለ ቅራኔ እንኳ ይኸው በስድስት ሳምንት ውስጥ ተፈቶ የለምን?

ልናገረው ይቀፈኛል እንጅ ስለቅንጅት የቤት ውስጥ ችግር ሰው የሚያትተው ብዙ ነው። በኃሀይሉና በብርሀኑ መሀከል ያለ አለመጣጣም ነው፤ የብርሃኑም የኃይሉም የሥልጣን ጉጉት አለበት፤ የኃይሉ ግትርነት ነው፤ የብርሀኑ አለመጨበጥ ነው፤ የመኢአድና የቀስተ ደመና ተቀናቃኝነት ነው፤ የገንዘብ ንኪኪ ነው፤ የለም የኢሕአዴግ እጅ አለበትና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

ከመጨረሻው ልጀምርና ያንዱ ወገን በሌላው ላይ ጥላሸት ለመቀባት ከሚያደርገው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ባሻገር አንተም ሆንክ ብርሃኑ በኢሕአዴግ የሚሸነገል ዓይነት ርካሺ ህሊና እንደሌላችሁ እውቅ ነው። ሁለታችሁም ከዚያ የርካሽነት ደረጃ ያለፋችሁ ናችሁና። የገንዘብ ንክኪ የሚባለውም አልባሌ ወሬ ለመሆኑ እኔ ራሴ ማረጋገጫ አለኝ። እነዚህን ሁለቱን አሉባልታዎች ካወጣን ግን ችግሩ በሁለት ግለሰቦች መሀከል የተፈጠረ አለመጣጣም እንጅ ከ80 ሚሊዮን ሕዝብ ጉዳይ ጋር የማይገናኝ ሆኖ እናገኘዋለን። በሌላ አነጋገር ቅንጅትና ደጋፊዎቹ ፈረንጆቹ እንደሚሉት የኢጎ አለያም ደግሞ የኋላቀርነት መገለጫ የሆነው የግትርነት ሰለባ ሆነናል ማለት ነው። ታዲያ ይህ አንጀትን ካላቆሰለ ምን ሊያቆስል ይችላል? ታዲያ ይህ መሳቂያና መሳለቂያ ካላስደረገን ምን ሊያስደርገን ይችላል?

ውድ ወንድሜ!

ፖለቲካ ሁሉም በኪሣራ የሚለያዩበት የዳተኞች ጨዋታ አይደለም። አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ የሚሆንበት የፖለቲካ ቀመርም አይደለም። “እኔ ቅዱስ እሱ እርኩስ” ከሚል እይታ የሚጠነጠን የፖለቲካ ስትራቴጅ ደግሞ የኋላ ቀርም ኋላቀር ነው። ልብ ብለን ካየነው ለሦስተኛው ዓለም ኋላቀርነትና ሥልጣንን በደም የማሸጋገር አስከፊ ባህል መነሻዎቹ እነዚህ አመለካከቶች ናቸው። ቀሪዎቹ ችግሮቻችን የነዚህ ምንዛሪዎች እንጅ ሌላ አይደሉም።

“እሱ እንዲህ ብሎ! እሷ እንዲያ ብላ” እየተባባላችሁ ከፈጠራችሁት በቀላሉ ከሚነሳ የፖለቲካ አቧራ ባሻገር ሁለታችሁም ወገኖች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላችሁ የጋለ ስሜትና በቅንጅት ራዕይ ላይ ያላችሁ አቋም ቅንጣት እንኳ እንደማይለያይና እንዳልተቀየረም እናውቃለን። ታዲያ ይህ ሁሉ ጭቅጭቅና ውዝግብ፤ ይህ ሁሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰቆቃ ማራዘም፤ ይህ ሁሉ ወገንን ማሳዘን በታሪክ ውስጥ ክቡር ቦታን ያስገኛል? ታሪኩም ይቅርና ከህሊናስ ፀፀት ያድናል?

ለሀኪሞች ብቻ ማን እነደሰጣቸው አላውቅም እንጅ “የበሽታውን መንስዔ ለይቶ ማወቅ የመፍትሔውን አጋማሺ ማግኘት ነው” የሚል ብሂል አላቸው። እኔ ግን በፖለቲካና በዕለት-ተለት ኑሮም እንዲሁ ይመስለኛል።

ለቅንጅት፤ ለመሪዎቹና በሚሊዮን ለመቆጠሩ ደጋፊዎቹ የወቅቱ አጣዳፊ ተግባር የፓርቲውን የውስጥ ችግር መፍታት ብቻ ነው እላልሁ። ሰፊውና ውስብስቡ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም፤ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንኳ አይደለም። እነዚህ ክቡር እሴቶች እውን የሚሆኑት መሪ፤ ተቆርቋሪና አራማጅ ፓርቲ ሲያገኙ ብቻ ነውና።

የቅንጅት አመራር በመሀከሉ ያለውን መለስተኛ ቅራኔ በውይይት ለመፍታት አለመቻሉ ለሕዝቡ የሀዘን ምንጭ መሆኑንና በርካታ ንቁ ደጋፊዎች ወደ ገለልተኝነት እንዲሸጋገሩ ምክንያት መሆኑን አለመገንዘብ ስህተት ይመስለኛል። ለኢሕአዴግና በቅንጅት ለሚቀኑ ለሌሎች ፓርቲዎች ደግሞ የመዘባበቻ መሣሪያ እንደሆነላቸው እውቃለሁ። ስለዚህ ነው ለቅንጅት ይህን አንገት የሚያስደፋ ሁኔታ ከመቀየርና ደጋፊዎቹን እንደገና በትግሉ መስክ ከማሰባሰብ የበለጠ አጣዳፊ ተግባር ሊኖር አይችለም ያልኩት።

ፖለቲካ የድርድርና የሰጥቶ መቀበል ልጅ ናትና ያለፈውን ወደኋላ ትታችሁ ሁሉንም አሸናፊ በሚያደርግ ቀመር ውስጥ ችግሮቻችሁን እንድትፈቱ አይምሮአችሁም ልባችሁም ይከፈት ዘንድ እጸልያለሁ። በፖለቲካው ዓለም ወቅታዊነት ወሳኝ ነውና የሚጠፋ ደቂቃ እንኳ ሊኖር እንደማይገባ አስገንዝቤ እሰናበትሀለሁ።

ከማክበር ሠላምታ ጋር
ኩችዬ
ማርች 1 ቀን 2008 ዓ/ም

ማስታወሻ፡
ቃሊቲ በእስር እያለህ የጻፍኩልህን ደብዳቤ ቅጅ አያይዠዋልሁ

No comments: