Friday, May 29, 2009

"መሬት የመቸብቸቡ ጉዳይ! "

ችስታ የመታቸው አገሮች ሰፋፊ መሬታቸውን ለውጭ መንግሥታት በገፍ የመቸብቸባቸው ፈሊጥ በዓለም መድረኮች አነጋጋሪ ሆኗል። በኛው አካባቢም ብዙ ንትርክና ቁጣ እንደጫረ ተረዳሁና ጉዳዩን መመርመር ጀመርኩ። ሳያጣሩ ወሬ ሳያነቡ መምሬ መሆን አጉል ነውና በመጠኑም ቢሆን አንብቤ ያገኘሁትን ላካፍላችሁ።

ሳኡዲ፤ ኤሚሬት፤ ኳታር፤ ኩዌት፤ ግብጽ፤ ሊቢያ፤ ቻይና፤ ደቡብ ኰርያና የመሳሰሉትን አገሮች የእህል ዋጋ ሰማይ እየነካ መሄዱ የምግብ ሴኪውሪቲ እያሳጣቸው ነው። ባዮ-ፊውል ለማውጣት ሲሉ ፈረንጆቹ ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን እህል መቀነሳቸውም ሼኮቹን ያስደነቀ አይመሰለኝም።

ይሁን እንጅ እንደ ሳኡዲ ያሉትን የናጠጡ ሀብታሞች ያሳሰባቸው ከላይ የተጠቀሰው ብቻ አይደለም። ሳውዲዎች በማይታመን ዋጋም ቢሆን እህል በበረሀ ውስጥ ያመርታሉ። የሳውዲ እርሻዎች ለብሔራዊ ኩራት ምንጭ ሆነው ይቆዩ እንጅ በከርሰ-ምድር ያለውን የውሀ ክምችት ክፉኛ በሟሟጠጥና አካባቢን በመበከል ረገድ ጋውፋህ (የተሲያት እንቅልፍ) የሚነሱ ዓይነት ሆነውባቸዋል። በኢትዮጵያው ኮንትራት የተመረተው ሩዝ በታላቅ ሥነ-ሥርዓት ታጅቦ ለሳኡዲው ንጉሥ ሲቀርብላቸው በፈገግታ የተሞሉት ያለምክንያት አልነበረም። ለምን አይሞሉ? ርስቱ ከወንዝ ባሻገር፤ የተገኘው በነፃ፤ የኤክስፖርት ታክስ አይከፈልበት፤ የሚሟጠጠው የሌላ አገር ውሀ፤ የሚመረዘው የሌላ አገር መሬት።

ከወዲሁ ላስጠንቅቃችሁና የውጭ ኢንቬስትመንት ለዕድገት እጅግ አስፈላጊ ግብአት ነው ከሚሉት ወገን ነኝ። ስለሆነም የመሬቱን ኮንትራት የማየው በ “ጠርጥር” መነጽር ተጋርጄ አይደለም። ለዚህም ነው አዲስ ዓይነት “የጅ-አዙር ቅኝ አገዛዝ” ወዘተ የሚለውን ዝባዝንኬ ክርክር የማልስማማበት። አገርም ግለሰብም የሚፈርሙትን ውል በቅጡ ካሰቡበትና ጥቅማቸውን ለማስከበር በቂ ጥንቃቄ ካደረጉ የጅ-አዙርም የሌላም ዓይነት ቅኝ አገዛዝ ሰለባ አይሆኑም። ደ!

በነገራችን ላይ በመሬት ችብቸባው ንግድ የተሰማራችው ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሱዳን፤ ዛምቢያ፤ ታንዛኒያ፤ ኮንጐ፤ ሞዛምቢክ፤ ካምቦዲያ፤ ዩክሬን፤ ሰርቢያና የመሳሰሉት ጭምር ናቸው። ሩስያ አውስትራሊያና ብራዚልን የምያካክሉ የዳጎሰ ኤኮኖሚ ያላቸው ሳይቀሩ ከነሳኡዲ ጋር ሽር ጉድ እያሉ ነውና ያዲሱ ዓለም የኢንቬስትመንት ቄንጥ ይህ እንደሆነ እንወቅ። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያም ድርሻዋን ለማግኘት ብትሯሯጥ ልንገረም አይገባም - ኢንቬስትመንት ካፒታል እንደሷ የሚያስፈልገው አገር የለምና።

ታዲያ ችግሩ የት ላይ ነው? በጣም ጥሩ ጥያቄ። ችግሩ ያለው መሬት የሚቸበችቡት አገሮች ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በማያውቁ መንግሥታት ሥር የሚተዳደሩ መሆናቸው፤ አኮናታሪዎቹም ተኮናታሪዎቹም ሙስናን ባህል ያደረጉ መሆናቸው፤ የውል ዝርዝሩ ድብቅ መሆኑ፤ ኢንቬስተሩ ያመረተውን እህል ሙልጭ አድርጎ ወዳገሩ ወይንም ወደ ዓለም ገበያ የመውሰድ መብት እንዲኖረው መደረጉ ይገኙበታል። ይህ ብቻ አይደለም! ውሉ ስለከባቢ ዓየር መበከል፤ ስለብሔራዊ የውሀ ቋት መሟጠጥ፤ ስለነዋሪው ሕዝብ መፈናቀል ከመጨነቅ ይልቅ የኢንቬስተሩንና የውል ሰጨዎችን ኪስ በማሟሸት ላይ የተጣደፈ ነው የሚሉም ይበዛሉ። እኔ ማነኝና ነው አዋቂዎች የሚሉትን ላስተባብል የምሞክረው? እንቀጥል…

ከኢንቬስተሮቹስ ምን ይጠበቃል? ይህም ሌላ ጥሩ ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያን በሚመለከት ከሳውዲ ኢንቬተሮች ጋር የተፈረመው ውል በምስጢር ስለተያዘ ምን ዝርዝር እንዳለው አይታወቅም። ይህ ነው እንግዲህ ግልጽ ያለመሆን ጣጣ። ኢንቬስተሮቹ የሚሉት የሥራ ዕድል፤ ምርጥ ዘር፤ አዲስ ቴክኖሎጅ፤ ዘመናዊ ማኔጅመንት፤ ትምህርት ቤቶች፤ ክሊኒኮች፤ ይዘን እንመጣለን ነው። ከተጠቀሱት ጥቅሞች ኢትዮጵያ ምን ያህሉን እንዳገኘች የሚያውቅ ሰው ካለ ይንገረንና የትኞቹ ዕውንት የትኞቹ ደግሞ ባዶ ተስፋ እንደሆኑ መለየት እንችላለን።

እስከዚያው ድረስ ግን ከሌሎች አገሮች ያገኘነውን ተመክሮ መሠረት አድርገን መወያየቱ ክፋት የለውም። ሌሎች አገሮች ውስጥ የተቋቋሙ የ “መንግሥት-ለመንግሥት” ወይንም የ “መንግሥት-ግል” የርሻ ኮንትራቶች ብዙ ፋይዳ አሳይተው እንደማያውቁ ያለም ታሪክ ይመሰክራል። ለነገሩ መንግሥት የሚይዘው ነገር የት ቦታ ነው ፈይዶ የሚያውቀው? ባንጻሩ ደግሞ የውጭ የግል ኢንቬስተሮች ካገሬው የግል ኢንቬስተሮች ጋር የሚጀምሯቸው ፕሮጀክቶች ብዙ ውጤት ታይቶባቸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉን በጄ ከሚለው አባዜ እስካልተላቀቀ ድረስ የሳውዲውም ሌሎችም ፕሮጀችቶች ብዙ ዕድሜ እንደማይኖራቸው ከወዲሁ መመስከር ይቻላል።

ወደማጠቃለሉ ላምራ። ከላይ እንደጠቀስኩት የውጭ ባለካፒታሎች በደሀ አገሮች ውስጥ የእርሻ ሥራ ለማስፋፋት መሺቀዳደማቸው የዘመናችን ክስተት ነውና ልናቆመውም ልንሸሸውም አይገባም። ጥያቄው ኢንቬስተሮች ይግቡና አይግቡ ከሚለው ላይ አይደለም - ይህ ብዙ አያከራክርምና። ፍሬ ነገሩ ያለው እንዲህ ያለው ውል ሁለቱንም ወገን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የሚጠቅም ነው አይደለም ከሚለው ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ የግልጽነት ጥያቄ ወሳኝ ይሆናል። ያገሬው ኢንቬስተር ተሳታፊነት ወሳኝ ይሆናል። ብሔራዊ ጥቅም የማስከበሩ ጉዳይ ወሳኝ ይሆናል። ተገቢው የኤንቫይሮንሜንት ሕግ መውጣቱና ማስከበሪያ መሣሪያዎቹም መደራጀታቸው ወሳኝ ይሆናል። የውጭው ካፒታል የሚንቀሳቀስበት የሕግ ዳር-ድንበር መከለሉ ወሳኝ ይሆናል። ስለሚፈናቀለው ገበሬና በከብት-ርቢ ስለሚተዳደረው ሕዝባችን እጣ-ፈንታ በቅጡ ማሰብ ወሳኝ ይሆናል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የዴሞክራሲ የመልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት መስፈንን የግድ ይላል።

እነዚህ ሳይሆኑ ቀርተው የመንግሥት ቢሮክራቶች በግብታዊነትም በሌላ ተነሳሺነትም የሚያደርጉት ውሳኔና የሚፈራረሙት ውል የሚያስገኘው ጥፋትና ኪሣራ ነው። በቆቃ ሀይቅና በወንዞቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ሁኔታ አሳዝኖን ከሆነ ይኸኛው ደግሞ ከትውልድ ወደትውልድ የሚተላልፍ የሀዘንም ሀዘን ይሆናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የውሎቹን ዝርዝር የማወቅ መብት አለው።

Kuchiye@gmail.com

----------
(እንግሊዝ ለሚቀናችሁ፡ “The Economist” May 23, 2009 አንብቡ። ብዙውን ያገኘሁት ከዚያ ነው)

Tuesday, May 05, 2009

"ኤይድስ በዳያስፖራው ኢትዮጵያዊ መንደር! "

ከዲሲ ሕዝብ 3% ያህሉ በኤይድስ በሽታ የተበከለ ነው። አንዳንዶች ማዕከላዊ ቁጥሩ ከዚህም እጥፍ ይሆናል ይላሉ። የጥቁሩን ሕብረተሰብ ብቻ ነጥለን ብንወሰድ 7% የሚሆነው የበሽታው ሰለባ ሆኗል።

ዛሬ የኤይድስ አክቲቢስት መስየ የቀረብሁት በበቂ ምክንያት ነው። በውጭ ከሰፈረው ኢትዮጵያዊ ወገናችን አብዛኛው መቶኛ ዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የሚኖር ስለሆነ ሁኔታው በግለሰብም፤ በማህበረሰብም ደረጃ ሊያሳስበን ይገባል። ከዚያም አልፎ ሊያስደነግጠን ይገባል። በጤናው መስክ የተሰማራ ወዳጄ በኢትዮጵያዊው ህብረተሰብ ውስጥ የኤይድስ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን ያጫወተኝ አይቼበት ከማላውቀው ትከዜ ጋር ነበር። በሱ ግምት የሀበሻው ሕብረተሰብ ተነጥሎ ቢጠና የተለከፈው ወገን ከ 10% እንደማያንስ አልተጠራጠረም። በተለይ ወጣቱ አካባቢ።

የዋሺንግተን ዲሲው ኤች አይቪ ኤይድስ ሁኔታ የወረርሽኝ ያህል አስደንጋጭ ደረጃ ላይ ስለደረሰ የመንግሥትንና የሕብረተሰቡን ትኩረት እያገኘ ነው። በሀበሻው መንደር ግን ግንዛቤውም ድንጋጤውም ጎልቶ አለመታየቱ እጅግ ያሳስባል!

ከወዳጄ ጋር ጭንቅላቶቻችንን ለጥቂት ጊዜ አጋጨንና የሚከተሉትን ቁምነገሮች ልናካፍላችሁ ተስማማን። በዚህ ዓለም ላይ ባለማወቅ ከምናደርጋቸው ስህተቶች እያወቅን የምንፈጽማቸው በጅጉ እንደሚበዙ የሰው ልጅ ታሪክ የመሰከረው ነውና የምናውቀውንም እንደገና መማማራችን አስፈላጊ ነው። ከተወሰነ ፍጥነት በላይ መንዳት ቅጣት እንደሚያስከትል እያወቅን ቲኬት የተከናነብን ስንቶች ነን? በኤይድስ ላይ የሚደረግ ውይይትንም በዚሁ መልኩ እንየው።

ኤይድስ መሠሪና ፈሪ ጠላት ነው። አዕምሮአችን በመጠጥ ወይንም በፍትዎት የተዘናጋበትን ሰዓትና አሳቻ ቦታ መርጦ ያጠቃል። ስለሆነም መጠጥ መጠጣት ካለብን ልካችንን እንወቅ።
ፍትዎት እንደታንጎ ሁለት ደናሺ ይጠይቃል። እኔ ጥንቁቅ ነኝና ጓደኛየም ትንቁቅ ትሆናለች ማለት አይቻልም። ያልተጋቡ ጓደኞች ኮንዶም መጠቀምን ከጀግንነትና ከስልጡንነት ሊቆጥሩት ይገባል። የኮንዶም ፍትዎት ያለኮንዶም ከሚደረግ ፍትዎት እኩል እንደሚጥም አዕምሮአችን ይቀበለው። ባለትዳሮችም ቢሆኑ አንደኛው ወገን በምንም መነሻ ይሁን ስጋት አደረብኝ ካለ “እንመርመር ቀፈፈኝ” ማለትን መፍራት የለበትም። ሌላው ወገንም እንዴት ተደፈርኩ! ብሎ አካኪ ዘራፍ አይበል። ምርመራው ለሁለቱም ይበጃል፤ መተማመንና ፍቅርን ያጠናክራል።
ሀገር ቤትን እንፍራ። አዎን ያገር ቤት ጉብኝትን መፍራት ነው። ያገራችን ሴቶች ቀድሞውንም ቆንጆ መሆናቸው አንሶ አሁን ደግሞ ይበልጡን እያማሩና እያማለሉ ሄደዋል። ኢትዮጵያ በዓለም ከፍተኛ የኤይድስ ተሸካሚ ከሚባሉት አገሮች አንዷ መሆኗን ስንገነዘብ፤ ሥራ አጥነት ወጣቱን በፍትዎት ንግድ ውስጥ እንዲሰማራና የቤተሰብ ሀላፊነትን እንዲሸከም ያስገደደበት አገር መሆኑን ስናይ፤ “ረሀብ ባንድ ቀን ይገድላል ኤይድስ ፋታ ይሰጣል” የሚሉት አሰቃቂ ቀልድ የነገሰባት አገር ሞሆኗን ስንረዳ፤ ከልማት ይልቅ የቡና ቤቶች የክለቦችና የማሳጅ ፓርለሮች ኢንዱስትሪ እንደ እንጉዳይ የፈሉባት አገር መህኗን ስናስታውስ፤ ሙያ ይመስል አዲሳባ ባንኮክን ሆናለች እያለ የፍትዎት ቱሪዝምን የሚያሞግስ ትውልድ የበረከተበት አገር መሆኗን ስንረዳ ዳያስፖራውያን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን እንረዳለን። ዶላርንና የውሸት ትዳርን አሰፍስፈው የሚጠብቁ እነርሱ አደገኞች ናቸውና እንቆጠብ።

በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በኤይድስ ወረርሽኝ በከፍተኛ መቶኛ የተመታው አገር ቤት ጋር ባለው ንኪኪ እንደሆነ በድፍረት መናገር ይቻላል። በሌላው ያሜሪካ ክፍልና በሌላው ክፍለ ዓለም ያሚኖረውም ኢትዮጵያዊም ከዚህ መቅሰፍት የተከለለ አለመሆኑን መዘንጋት የለበትም።

ገለልተኛነታችን ሊጎዳን መሰለኝ። ሀበሾች ስንባል ከሌላው ስደተኛ ህብረተሰብ በበለጠ በራሳችን ማህበረሰብ ውስጥ ተከልለን መኖርን እንመርጣለን። ይህ ተፈጥሯዊ መነሻ ቢኖረውም ተቋሞቻችን የሚገባንን እንክብካቤና ትመህርት ከሚሰጡበት የዕእድገት ደረጃ ላይ ካልደረሱ ተጎጅዎች እንሆናለን። አሜሪካኖቹ ኤይድስን በሚያክል አደገኛ ጠላት ላይ በሚያካሂዱት ዘመቻ ላንሳተፍ ነው። በዚህ በሽታ የተጠመዱ ወገኖቻችን ተደብቀው እንዲኖሩና ራሳቸውንም ሌሎችንም እንዲጎዱ ሰበብ እየሆንን ነው። ሀበሻው ጋር አድረን ሀበሻው ጋር ውለን ሀበሻው ጋር እስካመሸን ድረስ እንዲህ ያለ አደጋ ይመጣል፡፤

እናስ ታዲያ ምን ይሁን? እናማስ ሀላፊነት እንውሰድ። በየግላችን መውሰድ የሚገባንን ርምጃ በሃላፊነት ስሜት እንወጣ። ልጆቻችንንም ሰብሰብ አድርገን ያለ መሽኮርመም በዚህ ጉዳይ ላይ መወያየት ነው። በሞት ፊት መሽኮርመምን ምን አመጣው?

የሀይማኖት የፖለቲካና የማህበራዊ ተቋሞችም ችግሩን እያዩ እንዳላዩ አይሁኑና ይህን መሠሪ ጠላት በመዋጋት ረገድ አመራር ያሳዩን። ሦስቱም ቢሆኑ ጤነኛ ሕብረተሰብ በሌለበት ሊጠነክሩና ሊከበሩ አይቻላቸውም። በንዲህ አይነት ቅዱስ ዘመቻ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ያሚያደርግ ተቋም ከበሬታም ያገኛል የአባላትና የደጋፊ መሠረቱንም ያሰፋል። ኤይድስ በርዕዮተ ዓለምና በሀይማኖት ቀኖና ላይ የሚያሾፍና የሚረታ ሴሰኛ ባላንጣ ነው።


ቁጥር ቀልባችሁን ያስገኝልን እንደሁ ትንሺ በቁጥር እናስደንግጣችሁ። ዊኪፒዲያ የተባለው ድርጅት ለአቅመ አዳም የደረስውን በኤይድስ የተለከፈ ሕዝብ እንዲህ ያስቀምጠዋል። ታንዛኒያ 8.8% ኬንያ 6.7% ኮንጎ 4.9% ኢትዮጵያ 4.4% ። የሲ.አይ.ኤው ርፖርት ደግሞ የኢትዮጵያውን ወደ 10-18% ይተምንና በ 2010ዓ/ም ደግሞ ከ19-27% እንደሚደርስ ያሳስባል።

እንግዲህ የዲሲው ኤይድስ መቶኛ ከሦስተኛው ዓለም መቶኛ መብለጡ ካላስደነገጠን ምን ሊያስደነግጠን እንደሚችል አናውቅም። ዲሲን ከሦስተኛው ዓለም ጋር እንመድበው ይሆን?

Kuchiye@gmail.com