Thursday, January 10, 2008

የኬንያው ምርጫ ምን ትምህርት ሰጠን?
ኩችዬ - January 10, 2008
kuchiye@gmail.com


በትናንትናው ዕለት “ዊልሰን ሴንተር” እና “ሴንተር ፎር ስትራቴጅክ ስተዲስ” የተባሉ ታዋቂ የምርምር ተቋሞች በተጭበረበረው የኬንያ ምርጫ ላይ ልዩ አውደ-ጥናት አካሂደው ነበር። ዋሺንግተን ዲሲ ሬጋን ማዕከል በተካሄደው በዚህ ዝግጅት ላይ በተንታኝነት የቀረቡት ግለሰቦች የዕውቀትና የልምድ አድማስ ከመቀመጫ ኖር ያሰኛል።

አምባሳደር ጆኒ ካርሰን (አሜሪካዊ፤ የናሺናል ኢንቴሊጀንስ ካውንስል የአፍሪካ ባለሙያና የረጅም ዘመን ዲፕሎማት)፤ ዶ/ር ጆል ባርካን (አሜሪካዊ፤ ፕሮፌሰር ኤሜሪቲዩስ፤ የዴሞክራታይዜሽንና የመልካም አስተዳደር ምሁር፤ የአፍሪካ ኤክስፐርት)፤ ዶ/ር ሴለስተስ ጁማ(ኬንያዊ፤ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ልማት ምሁርና የሳይንስና ቴክኖሎግይ ዳይሬክተር)፤ ዶ/ር ሚይና ካይ፤ (የኬንያ ሰብአዊ መብት ሊቀመንበርና የሃርቫርድ ምሩቅ) ስቴፈን ዴዋ (ኬንያዊ፤ በዩሲኤልኤ ስኮላር፤ በዓለም ባንክ የመልካም አስተዳደር ምሁር..)። በስብሰባው ላይ የተጋበዙት እንግዶችም በዓለም አቀፍ ግንኙነት፤ በደህንነትና በልማት ጥልቅ ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ነበሩ።

ይህን እንደመደርደሪያ አጣቀስኩት እንጅ ዓላማዬ በጉባኤው ላይ ከተነሱት ቂምነገሮች መሀከል ይጠቅማሉና ልናገናዝባቸው ይገባል ብየ የገመትኳቸውን ለናንተ ለማካፈል ነው። ሀተታ ላለማብዛት ባጫጭሩ እደረድራቸዋለሁ። የግል አስተያየቴን አልጨመርኩም፤ እንደወረደ አቅርቤዋለሁ ማለቴ ነው ባዲሳባዎቹ ቡና ወዳጆች ቋንቋ።

ይህን ያውቁ ኖሯል?
ኬንያ በአፍሪካ 5ኛዋ ትልቅ ኤኮኖሚ ናት፤ የዘይትና የሚነራል ሃብት ስሌቱ ውስጥ ካልገባ 1ኛ ትሆናለች ይባላል። ከብሔራዊ ገቢዋ 60% ያህሉ የሚመነጨው ከናይሮቢና አካባቢው ነው፤ 1ኛ የውጭ ምንዛሪ አስገቢ እንደሚታሰበው ቱሪዝም ሳይሆን ውጭ ከሚኖሩ ኬንያውያን የሚላክ ገንዘብ ነው፤ የውጭ ርዳታና ብድር ከኬንያን ብሔራዊ ገቢ 5% ያህል ነውና ኃያላን መንግሥታት ኬንያ ላይ ተጽዕኖ የማድረግ አቅማቸው የፈረጠመ አይደለም፤ ከ40 በላይ ጎሳዎች ሲኖሩ ታላላቆቹ ኪኩዩና ሉዎ ናቸው፤ ። ኬንያ መልካም የዴሞክራሲ ባህል የገነባችና መረጋጋት የሰፈነባት ተብላ ስለምትቆጠር በአካባቢው ዋነኛ ያሜሪካ ሽሪክን የዲሞክራሲ ቤተ-ሙከራ ናት።

የሰሞኑ (2008) ምርጫ።
ኬንያ ባለፉት 20 ዓመታት እየተሻሻለ የመጣ 3 ምርጫዎች አካሂዳ ነበር። የሰሞኑ ምርጫ ከመካሄዱ በፊትም ሁኔታዎች ተመቻችተዋል። (42 ነጻ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች፤ 3 ነጻ ቲቪ፤ በርካታ ሲቪል ሶሳይቲዎች፤ የሰለጠኑ የምርጫ ቦርድ ሠራተኞች ወዘተ…)። እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት ዴሞክራሲን ለማራመድ የበሰለ አየር እንደነበረ ነው። የአውሮፓ ማሕበር ብቻ 30 ቋሚና 90 ያጭር ጊዜ ታዛቢ አሰማርቷል።

ታያዲያ ምን ተፈጠረ?
በኬንያ ማህበረሰብ ውስጥ ውጥረቶችና ብሶቶች ሲከማቹ ቆይተዋል። (ባለውና በሌለው መሃከል የሚታየው ልዩነት፤ በክፍለሃገሮች መሃከል የተዛባ ልማት መኖሩ፤ በጎሳዎች መሃከል የሃብት አለመተካከል መስፈኑ፤ ባዲሱ ትውልድና በቆየው ትውልድ መሃከል የራእይ ልዩነት መኖሩና የመሳሰሉት)። ምርጫ ጣቢያዎቹ ከ6 ኤኤም እስከ 5 ፒኤም ተከፍተው ታዛቢዎች ባሉበት ቆጠራው ተጠናቀቀና ሣጥኖቹ እየታሸጉ ወደ ናይሮቢ ምርጫ ቦርድ ዋና መ/ቤት ተላኩ። ተወዳዳሪው ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ፓርቲ እንዳሸነፈ መርጠው በሚወጡ ዜጎች ቃለመጠይቅ እየተረጋገጠ መጣ። ይህም በሁለቱ ፓርቲዎች ደጋፊዎች አካባቢ ጭንቀትና መፋጠጥን እያስከተለ ሄደ። በቦርዱ ዋና ጽ/ቤት በተካሄደው ቆጠራ ኦዲንጋ በ320 000 ድምጽ እንደሚበልጡ የተረጋገጠ ቢሆንም የቦርዱ ሃላፊ ቤተመንግሥት ተጠርተው ኪባኪ አሸንፏል የሚል መግለጫ አውጣ ተብለው በደረስባቸው ማስፈራራት መግለጫውን አወጡ። ኺባኪም በይድረስ ይድረስ ፕሬዚዳንት ነኝ ብለው መሃላ ፈጸሙ።

የምርጫው መጭበርበር ያስከተለው መዘዝ።
በመንግሥትና በምርጫ ቦርዱ ላይ የነበረው ጥርጣሬ እየገነነ መጣና በመላ ኬንያ ሕዝባዊ አመጽ ተቀሰቀሰ። እስካሁን ከ 500 በላይ ህይወት የጠፋ ሲሆን በሁለት ሳምንታት ብቻ ኤኮኖሚው ላይ 1 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል፤ ይህም የኬንያ ኤኮኖሚ የቱን ያህል የዳበረ እንደሆነ ያመለክታል። ከሁሉም በላይ ግን አሳሳቢ የሆነው በዲሞክራሲ ግንባታ ጥረት ላይ፤ በኬንያ ሕዝብ መሃከል የፈጠረው ጠባሳ ነው። ሦስት ዓይነት የግድያ ወንጀሎች ታይተው ነበር… (ሀ) የግለሰቦች (ለ) በሚሊሺያ ዓይነት የተሰባሰቡ) (ሐ) የመንግሥት ወታደሮች በማናለብኝነት ግንባር ላይ በማነጣጠር የገደሏቸው

ምን መደረግ አለበት? ምሁራኑ ያቀረቧቸውን መፍትሔዎችና ያሰመሩባቸውን ቁምነገራም ነጥቦች ያለ ቅደም ተከተል አካፍላችኋለሁ።

  • ምርጫው አወዛጋቢና ከፍተኛ ውድድር የሚታይበት እንደሚሆን ከወዲሁ የታወቀ ቢሆንም ሁኔታውን የሚመጥን መከላከያ አልተደረገበትም
  • ወቅታዊው ጥያቄ የምርጫው አወዛጋቢነት ቢሆንም ለንዲህ ዓይነት ችግር መንገድ የሚከፍቱትን መሠረታዊ ችግሮች ምንጭ ለይቶ ማወቅና ማስተካከል ወሳኝነት አለው
    ሀ. “መንግሥት” የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ በአፍሪካና በሌሎች ኋላ ቀር አገሮች ፈላጭ ቆራጭና የበላይ ሆኖ የመታየቱ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ይህ በጅጉ መለወጥ አለበት።
    ለ. ፕሬዚዳንት ወንም ጠቅላይ ሚኒስትር የሚባለው ጽንሰ ሃሳብም ዘውድ መጫን ቀረው እንጅ በአፍሪካ “ግርማዊ ፕሬዚዳንት” ወይም “ግርማዊ ጠቅላይ ሚንስትር” የመባል ያህል ሥልጣን አለው። ይህ ሥልጣን በጅጉ መከርከምና ከሕግ አውጭውና ከፓርላማው ጋር መተካከል አለበት
  • የምርጫ ክልሎች (ብሎክስ) የጎሳ አሰፋፈር መሥመርን እንዲከተሉ መደረጋቸው ለግጭትና ለጎሳ ስሜት መቀስቀስ ሰብብ ሆኗል። ይህም አደገኛ አዝማሚያ መለወጥ አለበት
  • በጥቅም መተሳሰርና ጉቦኝነት የዴሞክራሲና የብሔርዊ ስምምነት መፈጠር ጠንቅ ናቸው።
  • የ2008 ቀውሶች የ2003 ምርጫ ውድቀቶች ቅጥያ ናቸው። አረም በወቅቱ ካልታረመ ለተደጋጋሚ ጥፋት መዳረጉን የምርጫው ውዝግብ አንድ ምስክር ነው
  • የመደራደርና ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት የስምምነት ባህል መዳበር ትልቁ ፈተና ነው። አክራሪዎችና ግትሮች ዋና የዕድገት ፀሮች ለመሆናቸው ተደጋግሞ ተረጋግጧል
  • የአሸናፊ-ተሸናፊ ቀመር ኋላ ቀር ነው። በምርጫ የተሸነፈውን “ለፍርድ ይቅረብ” እያሉ የማላዘን ባህል ፈጽሞ መጥፋት አለበት። ሲሸነፉ ሥልጣን አንለቅም የሚሉትም ለዚህ ይሆናልና። የተሸነፈው ቡድን 40% ያህል ደጋፊ ቢኖረው እንኳ ትልቅ መሰናክልና መዘዝ ሊያስከትል መቻሉን ልብ ብለን ተገቢውን ክብር እዲያገኝ ማድረግ ብልህነት ነው
  • ፓርቲዎች የጎሳዊ እንቅስቃሴ መደበቂያ እንዳይሆኑና ብሔራዊ አንድነትን እንዳይጻረሩ ነቅቶ መከላከል ይገባል
  • የቡድን ምብት የግለሰብ መብትን ያህል ትኩረት ያግኝ። ያፈጠጠ ችግራችን ነውና
  • በሁለቱም ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ አክራሪዎች ለኬንያ ችግር መነሻ ሆነዋል። አብዛኞቹ ውጭ አገር ብዙ ጥቅም ስላላቸው ዓለም አቀፍ ሕብረተሰብ በሩን ሊዘጋባቸውና የጉዞ ማዕቀብ ሊያደርግባቸው ይገባል።
  • ተመራጮችና ሹሞች ከባህላዊው “የበላይ ጠባቂነት” (ፓትሪያርካል) አመለካከት መላቀቅ አለባቸው። ያለችሎታውና ያለሚዛናዊነት ወገን የማሰባሰብ ኋላ ቀር ባህል ይቅር
  • ሕገ መንግሥቱ በቅኝ ገዥዎች ታሪክና በመሬት ይዞታ ላይ ያተኮረ ነው። የኢዱስትሪ የንግድና የሃያ አንደኛው ክፍለዘመን ቅኝት እንዲኖረው ሆኖ ሊስተካከል ይገባል።
  • “ሮል ሞዴል” መምረጥ ተገቢ ነው። ማሌዚያ የጎሳ ችግሯን ሁሉን በሚያቅፍና ዘመናዊ የኤኮኖሚ ሞዴል ፈታች። ብራዚል ናይጀሪያና ሌሎችም ምሳሌ ይሆናሉ። ቁምነገሩ ከጎሳ ባሻገር አዲስ ተስፋ የሚሰጥ የወጣቱንና የሥራ አጥነትን ችግርና በንግድና በኢንዱስትሪ ዙሪያ የሚያሰባስብ ሞዴል መፍጠር ላይ ነው።
  • በክልሎች መሀከል ያለውን ልዩነት ማባባስ ሳይሆን ማደብዘዝና ማጥፋት ላይ እናተኩር
  • በትውልዶች መሀከልም ያስተሳስብና የራዕይ አለመጣጣም አለና ይህም መገናዘብ አለበት። ከ25-40 ያለው ትውልድ ከታላላቆቹ ይልቅ የተማረና ሕይወቱን በትጋት ለመለወጥ የሚጓጓ መሆኑ አይዘንጋ። ወጣቱ በለጋነቱ የቤተሰብ ሀላፊ እየሆነ ስለመጣ እንዲያውም የምርጫ እድሜን ዝቅ ማድረግ ተገቢ ይሆናል።
  • የዲያስፖራው ኬንያዊ የገንዘብና የዕውቀት ምንጭ መሆኑ ቢታወቅም አገር ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ የጎሳ ስሜት ከሚያባብሱ ኢሜይሎችና ጽሁፎች ይቆጠብ
  • ሚዲያው ሁለት ስለት ያለው ጎራዴ ነው። ችግርን በማባባስ ረገድ አስተዋጻኦ ሊያደርግ ቢችልም መዘጋቱ ይበልጥ አደገኛ ነው። ርዎንዳ ውስጥ ነጻ ፕሬስ ሲጠፋና የርስ በርስ ጦርነት ሲጀመር ሕዝቡን ማስተማሪያ መገናኛ ጠፋና ሚሊዮኖች አለቁ
  • ዴሞክራሲ የሁለት ርምጃ ወደፊት የአንድ ወደኋላ ውጤት መሆኑ አያከራክርም። በየትኛውም አገር ታሪክ ማለት ነው። ስለሆነም የኬንያው ችግር ተስፋ-ቢስ ሊያደርገን አይገባም። ተመሳሳይ ችግር በኢትዮጵያም በናይጀሪያም በሌሎችም ታይቷል። እንዲያውም በኬንያ 20 ዓመት ያህል የተካሄደው ሠላማዊ የዴሞክራሲ ግንባታ ለኬንያም ላፍሪካም ትልቅ ምሳሌነት አለው።
  • ለኬንያው ችግር መፍትሔ ስንሻ እስካሁን የነበረውን ዘመን “የመጀመሪያው ሪፐብሊክ” ብለን መዝጋት እንችላለን። የቀሰምናቸውን ልምዶች መሠረት አድርገን ሁለተኛውን የኬንያ ሪፐብሊክ እንጀምራለን።
  • የመጀመሪያው ተግባራችን አክራሪ አቋሞችን መወርወርና ለሕዝብና ለብሔራዊ አንድነት ሲባል ቀና ድርድር ማካሄድ ነው። ለዚህ ደግሞ ኬንያውያንና ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በእምቢተኞች ላይ ግፊት ማድረግ አለባቸው።
  • የረብሻ አለመኖር የመረጋጋትና የሠላም መስፈን ምልክት አለመሆኑን አንዘንጋ። ችግሮች ላይ በቅድሚያ መዝመትና ቅራኔዎችን ከወዲሁ መፍታት ትልቁ ብልህነት ነው።

    ማሳሰቢያ፡
    የኬንያው ችግር ለኢትዮጵያውያን ችግራቸው ነውና ሊያሳስበንም በተቻለ መጠን ርዳታ ልናደርግበትም የሚገባ ነው። ኬንያ የሚገኘው መፍትሔም ለሀገራችን ምሳሌነት አለውና በቅርብ ልንከ