Thursday, November 15, 2007

የቅንጅት መሪዎች የሚመለሱት በፍቅር ወደተሞላው የወገናቸው እቅፍ ውስጥ ነው!

የ 97 ምርጫ ይዞት ከመጣው ተስፋም ሆነ ካስከተለው ፀፀት ያልተማረ የለም ቢባል ስህተት አይሆንም። “ፕሮግራሜ በመላው ኢትዮጵያ ተቀባይነት አለው፤ ለሕዝብና ከሕዝብ ጋር የቆምኩ ነኝና ምርጫ ቢከናወን በአሸናፊነት እወጣለሁ” ብሎ ያስብ ከነበረው ከኢሕአዴግ የበለጠ ከዕንቅልፍ የሚገፈትር ማንቂያ አግኝቷል። ለዚህም ነበር በምርጫው የደረሰበትን ኪሳራ ለመገምገም ካድሬዎቹን፤ የደህንነት ሠራተኞቹንና ሌሎች በመላ ሀገሪቱ የበተናቸውን ባለዳረጎቶች በምርጫው ማግሥት ሰብስቦ ማፋጠጥ የጀመረው። በዚያው ሰሞን በየወረዳውና በየነጥብ ጣቢያው ሳይቀር ሕዝቡን ሰብስቦ “ምን በድለናችሁ ነው እንዲህ የገፋችሁን?” እያለ ተማጸነ። ገበሬውና ነጋዴው፤ ተማሪውና አስተማሪው፤ ከተሜውና ገጠሬው ብሶታቸውን ባንድ ድምጽ አሰሙ…..

“ሕዝብን የመለያየት ፖለቲካችሁን አቁሙ!”
“ያንድ ወገንን የበላይነት በሌሎች ላይ ለመጫን የምትፈጽሙት ዓይን ያወጣ ነውር ያብቃ!”
“ካድሬዎቻችሁ ወታደሮቻችሁና ሹሞቻችሁ የሚያደርሱት ወከባ ኢትዮጵያዊነታችንን አጠራጥሮናል!”
“መሬትን የፖለቲካ መሣሪያ አታድርጉ!”
“ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን ይከበሩ”
“ነጻ ፍርድ ቤቶች፤ ነጻ ምርጫ ቦርድ፤ ነጻ ሠራዊት፤ ነጻ ፕሬስ… !” ወዘተ

ገዥው ፓርቲ እነዚህን የሕዝብ ቅሬታዎች አላዳመጠም ማለትና ግዙፍ ስህተቶች መፈጸሙ አልረበሸውም ማለት ጭራሹን ማሰቢያ አዕምሮ አልፈጠረበትም ማለት ይሆናልና እዚያ ድረስ መሄድ ስህተት ነው። ጥያቄው መሆን ያለበት በስህተቶቹ ላይ የርምት ርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል ሃቀኛነት፤ ወኔና የፖለቲካ ብስለት አለው የለውም ከሚለው ላይ ነው። የታሪክን ማህደር ስንመረምር በመሣሪያ ኃይል ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከስህተታቸው ተምረው ለዴሞክራሲ ጥርጊያ መንገድ የከፈቱ ጥቂቶች ናቸው። እነዚህ ወገኖች ራሳቸውን የማታለል አባዜና “ሁሉም አልጋ ባልጋ ነው” የማለት በሽታ ያጠቃቸዋል። ኢሕአዴግ ለዲሞክራሲ ጥርጊያ ከከፈቱት የታሪክ ክበብ ውስጥ የመመደብ ዕድል እንዲገጥመው የማይመኝ ያለ አይመስለኝም። እስከዚያው ግን መንግሥት ከ 97 ምርጫ ተምሬ በተወካዮች ምክር ቤት፤ በምርጫ ቦርዱና በሌሎች ተቋሞች ውስጥ ማሻሻያ አድርጌአለሁ የሚላቸው ርምጃዎች እጅግ ቢበዛ የይስሙላ አለዚያም ማደናገሪያዎች ናቸው። የሚጠቅሳቸው ማሻሻያ ተብየዎች ቀናነት የሚጎድላቸው፤ በፈንጅ የታጠሩና የዴሞክራሲን እድገት ፈቀቅ እንኳ የማያደርጉ ናቸው።

ቅንጅትና መሪዎቹ የፍትህ እጦት ሰለባ ሆነው ለሁለት ዓመታት በእስር የተንገላቱት የሠላማዊ ትግል መርሆችን ተከትለው ዲሞክራሲን ለማምጣት ስለታገሉ ብቻ ነበር። መላ ቤተሰባቸውና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከነርሱው ጋር ታስሮ ከነርሱ ጋር ተፈቷል ማለት ይቻላል። ራሱ ኢሕአዴግም ከህሊና እስር ለመውጣት ዕድል አግኝቷል ማለት ይቻላል።

የተከፈለው የሕይወት፤ የመንፈስና የማቴሪያል መስዋዕትነት ዋጋ የሚያገኘው በሀገራችን የሰፈነውን የውጥረትና የጥርጣሬ አየር አስወግደን የሚቀጥለውን የዲሞክራሲ ምዕራፍ በአዲስ ቀለም ለመጻፍ በቀና ልቦና መሥራት ስንጀምር ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ መነሻውም መድረሻውም በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረግ ስልጡን ፖለቲካ ነውና የስጋት፤ የበቀልና የጥላቻ መንፈስን ወርውረን ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበትን የፖለቲካ ቀመር ማስላት አለብን። በሠላማዊ ትግል የምናምን ሁሉ ከዚህ ውጭ ፖለቲካ ሊታሰበን አይችልም። የሠላም አየርን ለሚማለድ ሕዝባችንም ሆነ በተደጋጋሚ ሰቆቃ ለተጎሳቆለች ውድ ሃገራችን ከዚህ የከበረ የሚሊኒየም ገጸበረከት ልንሰጣቸው አንችልም።

ምንጊዜም መዘንጋት የሌለብን ቁም ነገር ግን የዜጎችን መብት የሚያረጋግጥ መልካም አስተዳደር ከሌለ ብሔራዊ ደህንነት እንደማይኖር ነው። ለዚህ ደግሞ የመልካም አስተዳደር መሠረቶችን መገንባትና ማጠናከር አማራጭ የለውም። ከተጽእኖ ነጻ የሆኑ ፍርድቤቶች፤ ሕግ አውጭውና ሕግ አስፈጻሚው አንዱ ሌላውን የሚቆጣጠርበት ሥርዓት፤ የብዙሃን ፓርቲዎች መቋቋም፤ ሕገ መንግሥትን ማክበር፤ የንግግርና የመሰብሰብ ነጻነትን ማክበር፤ ዜጎች በሠላም ሠርተው የሚገቡበት፤ ብልጽግናና ደስታን የመሻት ተፈጥሮዋዊ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉበት የፖለቲካ አየር መፍጠር ግዴታ ነው።

ቅንጅትና መሪዎቹ ከላይ የተጠቀሱትን ቋሚ እሴቶች ለመገንባት በሚደርግ ብሔራዊ ጥረት ውስጥ ከሁሉም ወገኖች ጋር ለመሥራት ቀና መንፈስ ብቻ ሳይሆን ቁርጠኛነቱም እንዳላቸው አስመስክረዋል። የትናንቱ ጥፋትና ጉስቁልና ከትምህርት ሰጭነቱ ባሻገር ሚዛን የሚደፋ ፋይዳ የለውምና ዞር ብለው ወደኋላ የማየትና የማላዘን ፍላጎት የላቸውም። ይህንንም ዋሺንግተን ዲሲ ሴፕቴምበር 16 ቀን 2007 ባደረጉት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ አረጋግጠዋል። የሃገራችን አጣዳፊ አጀንዳዎች መላ ጊዜያችንን፤ ጉልበታችንንና ዕውቀታችንን በዛሬው ችግሮቻችንና በነገው ብሩህ ተስፋችን ላይ እንድናተኩር የሚያስገድዱ ናቸው።

በአንጻሩ ደግሞ ኢሕአዴግ አንዳንድ መሰናክሎችን እዚህና እዚያ እየወረወረ፤ እርባና የሌላቸው የሕግና ያስተዳደር ሰበቦችን እየጠቀሰ የብዙ ሚሊዮኖችን ሠላማዊ ፓርቲ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያደርገው አሰልች እንካስላንቲያ ኢሕአዴግንም ሃገርንም እንደማይበጅ ከታሪክ ሊማር ይገባል።

የቅንጅት መሪዎች ዓለም አቀፍ ተልዕኳቸውን አጠናቀው ወደሃገራቸው እየተመለሱ ባሉበት በዚህ ሰሞን መንግሥት ለሰብአዊ መብትና ለዲሞክራሲ ግንባታ ያለው ተአማኒነት በገሃድ ይመዘናል። የቅንጅት መሪዎች የሚመለሱት ወደሞቀውና በፍቅር ወደተሞላው የወገናቸው እቅፍ ውስጥ ነው። የሚያራምዱት የሠላማዊ ትግል፤ የብሔራዊ እርቅና በመቻቻል ላይ የተመሠረተ ሁሉን-አቀፍ የዲሞክራሲና የግንባታ አጀንዳ ነው። የሚቀነስም የሚደመርም ስውር አጀንዳ የላቸውምና ኢሕአዴግ ቡናውን አሽትቶ በቀናው ጎዳና መጓዝን ይምረጥ እንላለን።

የኢትዮጵያ ትንሣኤ አሁን ነው!

kuchiye@gmail.com